ሀገሬ ቲቪ

ሮበርት ሙጋቤ

በሙሉ ስማቸው ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ተብለው የሚጠሩት ሰው በቀድሞ ስሟ ደቡብ ርሆዴሽያ ተብላ የምትታወቀው ዚምባብዌን ከነጻነቷ በኋላ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስተሯ በመሆን ለ37 ዓመታት መርተዋታል።

የማርክሲዝም እና የጥቁር ብሄርተኝነት አቀንቃኝ የነበሩት ሙጋቤ በዚምባብዌ የነጻነት ትግል እንቅስቃሴ ውስጥም የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የሀገራቸው ብቸኛ መሪ ሁነው አራት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ዚምባብዌን አስተዳድረዋታል።

የብዙዎችን ትኩረት መሳብ የቻሉ መሪም ናቸው።ሮበርት ሙጋቤ የተወለዱት የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችው በደቡብ ርሆዴሽያ(ዚምባብዌ) ኩታማ በተባለ ስፍራ በ1916 ዓ.ም. ነበር።

አባታቸው አናጺ የነበሩት ሙጋቤ በካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት በመምህርነት ሰልጥነዋል። በደቡብ አፍሪካ ፎርት ሃሬ ዩኒቨርሲቲም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

በዚያም ፖለቲካዊ ተሳትፎን ጀምረዋል። በጋናም ቢሆን ቆይታ የነበራቸው ሙጋቤ በዚያው የመጀመሪያ ሚስታቸው ሳሊ ሃይፍሮንን አግኝተዋል።

በ1950ዎቹ መጀመሪያ ሙጋቤ የነፃነት አቀንቃኝ የሆነውን ናሽናል ዲሞክራቲክ ፓርቲን(NDP) ተቀላቀሉ። ከዓመት በኋላም ፓርቲው በመታገዱ ዚማባብዌ አፍሪካን ፒፕልስ ዩንየን (ZAPU) ወደ ሚል ስያሜ ተሻሽሏል። ከሁለት ዓመት በኋላም ሙጋቤ ይሄንንው ፓርቲን ለቀው የዚምባብዌ የአፍሪካ ብሄራዊ ህብረት(ZANU)ን ተቀላቅለዋል።

በሀገራቸው የነጭ ጥቂቶች የበላይነት ያስቆጣቸውቅ የነበሩት ሙጋቤ ለጥቁር ብሄርተኝነት አቀንቃኞች ብዙሃን ጥቁሮች የበላይ የሆኑበት አስተዳደርን የመመስረት ጥሪን ያቀርቡ ነበር። የዓመጽ ንግግር አድርገዋል በሚል በ1956 ዓ.ም. ታስረው የዕድሜያቸውን አስር ዓመታት በእስር ለማሳለፍ ተገደዋል።

ፓርቲያቸው ዛኑ በርሆዴሽያ የቅኝ ግዛት አስተዳደር እገዳ የተጣለበት ሲሆን ሙጋቤን የቅኝ ግዛት አስተዳደሩ አስሯቸዋል። በእስር ሳሉም በርቀት በመከታተል በህግ ዲግሪ አግኝተዋል። በዚያው በእስር እያሉም በ1960ዎቹ አጋማሽ እንደ ዛኑ መሪነታቸው መፈንቅለ መንግስትን መርተዋል።

በ1966 ዓ.ም. ሙጋቤ ከእስር ተፈተዋል። በርሆዴሽያ በጥቁር ብዙሃን እና በነጭ የበላይነት አስተዳደር መካከል በነበረው የርስ በርስ ጦርነት ሙጋቤ የፓትርዮቲክ ፍሮንት(PF) መሪ ከነበረው መሪ ንኮሞ ጋር በጋራ መሪ ነበሩ።

ፒኤፍ በጎረቤት ዛምቢያ፣ ሞዛምቢክ እና አንጎላ በመነሳት የደፈጣ ውጊያውን አጧጡፎ ነበር። ኋላም ጦርነቱ ሲጠናቀቅ የቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ ፓርላማ አዲስ በብሪቴይን የሚታይ ምርጫ ለማካሄድ ተገደደ። የሙጋቤ ፓርቲ ዛኑ ፒኤፍ (ZANU-PF) የሚል ስያሜን ይዟል። ከሌሎች የጥቁሮች ፓርቲዎች ይልቅ ድልን ከተጎናጸፈ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነዋል።

ሙጋቤ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ለዚምባብዌ ኢኮኖሚ በጊዜው አስፈጊ የነበሩትን የቀሩትን ነጮች ገበሬዎች እና ነጋዴዎች የማጽናናት አካሄድ ተከትለዋል።

ነጮች የሚወከሉበትንም የፓርላማ ስርዓት ለመመስረት ሞክረዋል። ጎን ለጎንም ደመወዝ ከመጨመር ጀምሮ፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማሻሻል እና የምግብ ድጎማ በማድረግ የጥቁር ዚምባብዌያውያንን ኑሮ ለማሻሻል ርምጃዎችን ወስደዋል።

በ1980ዎቹ ሁለት ጊዜ ተመርጠዋል። በ1990 ዓ.ም. ደግሞ ምንም እንኳን ለሀገሪቱ ማዕድናት ቋምጠው ነው የሚሏቸው ባይታጡም የዚምባብዌ ጦርን ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የርስ በርስ ጦርነት ልከዋል።

በአስተዳደር ዘመናቸው በተቀሰቀሰ አመጽ በነጮች ተይዘው የነበሩ እርሻዎች የተወረሩ ሲሆን ነጮች ከዚማባብዌ እንዲሸሹም ምክንያት ሆኗል። የሀገሪቱ የንግድ እርሻ መቀዛቀዝም ለከፍተኛ የዋጋ ንረት እና የምግብ እጥረት ዳርጓታል። የጎሳ ግጭቶችም ፈተናዎቻቸው ነበሩ። የዚምባብዌ ኢኮኖሚም ፈተና ውስጥ ወድቋል።

የማርክሲዝም አቀንቃኝ የነበሩት ሙጋቤ የምዕራባውያኑን አካሄድ በመወረፍም ይታወቃሉ። ስልጣንን ለመልቀቅ ባላቸው እምቢተኝነት የሚተቹት ሙጋቤ ዚማባብዌን ከፓርልያመንታሪ ዴሞክራሲ አንድ ፓርቲ ሶሻሊስት ሀገር የመቀየር ህልም ዓላማ ነበራቸው ይባልላቸዋል። ከ37 ዓመታት የስልጣን ቆይታ በኋላ ለኤመርሰን ምናጋግዋ ስልጣናቸውን ለቀዋል። በ95 ዓመታቸውም በሞት ተለይተዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-09-06