ሀገሬ ቲቪ

የምዕራባውያኑ ድጋፍ የነበራችው የኮንጎ አምባገነን

የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን ካገኙ በኋላ አምባገነን መንግስታት አላጧቸውም፡፡ ከነዚህ ሀገራት ደግሞ በማእድን ሀብቷ የበለጸገችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አንዷ ነች።

ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ የተባሉት ሰው ሀገሪቱን ለ32 ዓመታት መርተዋል። ሞቡቱ በአምባገነንነታቸው በዜጎቻቸው ላይ በመጨከን የሚታወቁ መሪ ቢሆኑም የምእራባውያኑን ድጋፍ ያላጡ መሪም ናቸው።

ዘመኑ የቀዝቃዛው ጦርነት የጦፈበት መሆኑ ምዕራባውያኑ እንዲያግዟቸው ምክንያት ሆኗል። እኒህ ሰው በሞት የተለዩት በዛሬዋ እለት በ1989 ዓ.ም. ነበር። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።

ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ የተወለዱት የቤልጅየም ኮንጎ ተብላ ትጠራ በነበረችው ኮንጎ በ1923 ዓ.ም. በሊሳላ ነበር። ከ1957 ዓ.ም. ጀምሮ የሀገሪቱን ስልጣን በመፈንቅለ መንግስት ከተቆጣጠሩ በኋላ ለ32 አመታት ከነአምባገነንነታቸው በስልጣን ላይ ቆይተዋል።

ትምህርታቸውን በሚሽን ትምህርት ቤት የተከታተሉት ሞቡቱ በ1940ዎቹ መጀመሪያ በቅኝ ገዥዋ ቤልጂየም የኮንጎ ጦር ውስጥ ስራ ጀምረዋል፡፡ ከጸሃፊነት የጀመሩት ሞቡቱ እስከዋና ሃምሳ አለቃነት ማእረግ ደርሰዋል።

ይሄው ማእረግ ለአፍሪካውያን ክፍት የነበረው ትልቁ ማእረግ ነበር። ለሊዮፖልድቫይል ጋዜጣም ይጽፉ ነበር። ኋላም በ1940ዎቹ መጨረሻ የእለታዊው ኤል አቬኒር ጋዜጣ ሪፖርተር ሆነዋል። ኋላም የዊክሊ አክችዋሊቲስ አፍሪካነስ አዘጋጅ ሆነዋል፡፡

ሞቡቱ በህትመት ሚዲያው በነበራቸው ተሳትፎ ከኮንጎ የብሄራዊ እንቅስቃሴ መሪ ፓትሪስ ሉሙምባ ጋር ግንኙነት ነበራቸው። የኮንጎ ብሄራዊ እንቅስቃሴ (MNC) በ1950 ዓ.ም. ከተመሰረተ በኋላም ሞቡቱ ፓርቲውን ተቀላቅለዋል።

ስለኮንጎ ነጻነት በቤልጅየም ብራሰልስ በነበረው ድርድር ፓትሪስ ሉሙምባን ተክተውም ተደራድረዋል። በጊዜው ሉሙምባ በነበራቸው የነጻነት እንቅስቃሴ ታስረው ነበር። ሞቡቱ ጠንካራ ማእከላዊ መንግስት ያላት ነጻ ኮንጎ እንድትመሰረት ሉሙምባ ያራምዱት የነበረውን ሃሳብ ደግፈው ተደራድረዋል።

ኮንጎ በ1952 ዓ.ም. ነጻነቷን አግኝታ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካሳቭቡ እና ፕሪምየር ሉሙምባ የጥምር መንግስት ሲመሰርቱ ሞቡቱ የሀገሪቱ መከላከያ ጸሃፊ ሆነዋል። በካሳቩቡ እና ሉሙምባ መካከል የነበረው የስልጣን ሽኩቻ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ሁነኛ ቦታ ላይ ነበሩ። ወደ ካሳቩቡ አድልተውም ሉሙምባ ከስልጣን እንዲወገዱ አደረጉ።

በሞቡቱ ሰራዊት ተይዘው የነበሩት ሉሙምባ ለመሞታቸው የሞቡቱ እጅ እንዳለበት ብዙዎች ያምናሉ። ሞቡቱ ከሉሙምባ መወገድ በኋላ የሀገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ ሆነዋል።

በ1957 አ.ም. በፕሬዝዳንት ካሳቭቡ እና ጠቅላይ ሚኒስተራቸው ሞይስ ሾምቤ መካከል የስልጣን ትንቅንቅ ሲያድግ ካሳቭቡን በመፈንቅለ መንግስት አስወግደው ፕሬዝዳንትነቱን ተቆናጠጡ።

የኮንጎ ኢኮኖሚ ላይም የካታንጋ የኮፐር ማእድንን በመንግስት እጅ በማስገባት እና ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት በመሆን ለውጥ አምጥተዋል። የሀገሪቱ ምግብን ከውጭ የማስገባት ፍላጎት ግን ጨምሯል።

በስልጣን ዘመናቸው ፖፑላር ሙቭመንት ኦፍ ሪቮሊውሽን(MPR) የተሰኘው ፓርቲ በሀገሪቱ ብቸኛው ህጋዊ ፓርቲ ሆኖ እንዲቆይ አድርገዋል። በርሳቸው አገዛዝ ላይ ተቃውሞ የነበራቸው በርካታ የኮንጎ ዜጎች እጣቸው መሰደድ እና መሰቃየት ብሎም መገደል ሆኗል።

በ1960ዎቹ በውስጣዊ አመጽ እና በመፈንቅለ መንግስት ሙኩራዎችም ውስጥ ሆነው ስልጣናቸውን ማስቀጠል ችለዋል። የሀገሪቱን እድገት በማምጣት ግን የተዋጣላቸው አልሆኑም። ሙስና፥ የአስተዳደር ብልሹነትም የስልጣን ዘመናቸው መልክ ነው።

የስልጣን ዘመናቸው የቀዝቃዛው ጦርነት የጦፈበት መሆኑ ኮሚዩኒዝምን ስለሚነቅፉ ብቻ የአሜሪካ እና ምእራባውያኑ ድጋፍ ነበራቸው፡፡ ፈላጭ ቆራጭ ስርዓት የነበራቸው ሞቡቱ ከፍተኛ የግል ሀብት በማካበት እና በጸረ ኮሚዩኒስት አቋማቸው የዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ ያልተለያቸው መሪ ነበሩ።

በ1980ዎቹ የቀዝቃዛው ጦርነት ጋብ ማለቱ ጋር ተያይዞ የምእራባውያኑን ድጋፍ አጡ። ጎረቤት ሀገራት ላይ ጣልቃ የሚገቡበት እጃቸው አጠረ። ታመሙም። በ1989 ዓ.ም. ስልጣናቸውን ርሳቸው ላይ ለተነሳው አመጽ መሪ ሎውሬንት ካቢላ ለቀቁ፡፡ በሞሮኮ በስደት ሳሉም በ1990 ዓ.ም. አረፈዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-09-07