
በሶማሊያ የምገባ ማዕከላት ከ 700 የሚልቁ ሕፃናት ሞሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት «ዩኒሴፍ» አስታውቋል።
በሀገሪቱ የዝናባ ወቅቶች ዝናብ አለመዝነቡን ተከትሎ በተከሰተው ድርቅ ነው እነዚህ ሕፃናት በምግብ እጦት ሕይወታቸውን ሊያጡ የቻሉት።
በመጪው ወራትም ዝናብ ላይዘንብ እናድርቁ ሊባባስ እንደሚችል ነው «ዩኒሴፍ» ያስታወቀው።
በ2003 ዓ.ም. በሶማሊያ በተከሰተ ድርቅ ከ 2 መቶ ሺ በላይ ዜጎች መሞታቸውን አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል።በዚያው ወቅት ሕይወታቸው ካለፈ ዜጎች ሰፊውን ቁጥር ሕፃናት ይሸፍናሉ።
በዚህ ዓመትም ታዲያ ከጥር እስከ ሐምሌ ባሉት ወራቶች ውስጥ በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የምግብ ማዕከላት 730 ሕፃናት መሞታቸው ተረጋግጧል።
ይሁን እንጂ ሪፖርት ያልተደረጉ የሞቱ ሕፃናት ሊኖሩ ስለሚችሉ የተጠቀሰው ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ነው በሶማሊያ የዩኒሴፍ ተወካይ ዋፋ ሰኢድ የተናገሩት።
እነዚህ ማዕከሎች ከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናት እንዲሁም እንደ ኩፍኝ ፣ ኮሌራ እና ወባ በመሳሰሉ የጤና እክሎች የሚሰቃዩ ሕፃናት አሉ።
ከቅርብ ወራት ወዲህ 13,000 ገደማ የሚሆኑ ሕፃናት በኩፍኝ ተጠርጥረው እንደሚገኙ ሪፖርት ተደርጓል።
ከእነዚህ ውስጥ 78 በመቶ የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ናቸው። በሶማሊያ የተገኙ የዩኒሴፍ ሹማምንቶች በርካታ ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ተመድ በበኩሉ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ለሶማሊያ የሚያስፈልገው ገንዘብ እንደጨመረ አስታውቋል። ተቋሙ ከያዘው 1.6 ቢሊዮን ዶላር 67 በመቶ ለድጋፍ ውሏል።
ነገር ግን አሁንም ቢኾን የነዚህን ሕፃናት ሕይወት ለመታደግ ተጨማሪ ገንዝብ እንደሚያስፈልግ ተነገሯል። አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰድ ከሚገመተው በላይ ሕጻናቶች ሕይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል ተሰምቷል።
በመላው ሶማሊያ 7.1 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የተፋጠነ የምግብ የሕክምና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
በአጠቃላይ በድርቁ የተጎዱ ዜጎች ለመታደግ 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በትላንትናው ዕለት ተመድ አስታውቋል። ይህ ገንዝብ ሊያገለግል የሚችለው እስከሚቀጥለው ዓመት የመጀመሪያ ወራቶች ድረስ ነው።
በሶማሊያ የተከሰተው ድርቅ በርካታ ሰዎች ምግብ እና የመጠት ውኃ ፍለጋ ከአካባቢያቸው እንዲሰደዱ አድርጓል። የቁም እንሣት በሜዳ ላይ እንዲረግፉ ምክንያት ኾኗል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-09-07