በአዲስ አበባችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የአፍሪካ ቴክ ኤክስፖ በዛሬው ዕለት ተከፍቷል። በኤክስፖው የሀገር ውስጥ እና የውጭ የቴክኖሎጂ ተቋማት እንደሚሳተፉበት ተጠቁሟል።
ከጳጉሜን 2 እስከ ጳጉሜን 4/ 2015 ዓ.ም. የሚካሄደው የአፍሪካ ቴክ ኤክስፖ በዛሬው ዕለት ተከፍቷል። ኤክስፖውን ጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ያዘጋጀው ሲሆን በአፍሪካ እና በሃገራችን የቴክኖሎጂ ተቋማት መካከል የልምምድ መለዋወጥን እንደሚያመጣ ተጠቁሟል።
የጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ኃይለ ኢየሱስ ስለኤክስፖው ዓላማ ይህንን ብለውናል።
ኤክስፖው የተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎችን እንደሚያካትትም አቶ ሳሙኤል ነግረውናል።
በኤክስፖው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር በለጠ ሞላ የቴክኖሎጂ ተቋማትን ማበረታታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ በኤክስፖው የሀገራችንም የአፍሪካም ተቋማት መሳተፋቸው ለሃገር ልማት እና ለስራ ዕድል ፈጠራም አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ጠቁመዋል። በኤክስፖው ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ድርጂቶች መካከልም ኤክስፖው ለልምድ ልውውጥ እና ራስን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቅማቸው ገልጸውልናል።
ተሳታፊዎቹ የተቋማቱን ትብብር ለማጠናከር ብሎም አዳዲስ ነገሮችን እንዲያመጡ ለማበረታታት መሰል ኤክስፖዎች ከዓመታዊነት በተጨማሪ በተከታታይ ቢካሄዱ ሲሉም መክረዋል። የኤክስፖው አዘጋጅ የሆነው ጆርካ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ሳሙኤል በየዓመቱ በአፍሪካ ሀገራት ዋና ከተሞች የሚካሄድ ነው ብለውናል።
በአብርሃም በለጠ
2022-09-07
