መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም በአሸባሪነት የተፈረጀው የህውሓት ቡድን አፋጣኝ ተኩስ አቁም ለማድረግ እና ወደ ድርድር ለመግባት ዝግጁ መኾኑንም አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም የሰላም ድርድሩ በቀድሞ የኬኒያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ አማካኝነት መኾን አለበት የሚል አቋም ይዞ ነበር። የህውሓት ቡድን ይህን ሊል የቻለው የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪ ኾነው በተሾሙት በኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ላይ እምነት እንደሌለው በማስታወቁ ነበር።
በትላንትናው ዕለት ታዲያ በአፍሪካ ኀብረት አማካኝነት የሚካሔደውን ድርድር እንደሚቀበለው እና ይህንንም ተልእኮ እንዲወጡ አቶ ጌታቸው ረዳን እና ጀነራል ጀነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ያከተተ ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙን አስታውቋል፡፡
አፍሪካ ኀብረት ከሚመራው ድርድር ተአማኔነት እንደሚኖረው እንጠብቃለን ብሏል ህወሓት። ይህ የድርድር ሒደት ታዲያ በኹለቱም ተደራዳሪ ወገኖች ተቀባይነት ያላቸው እና የጋራ እምነት ሊፈጥሩ የሚችል አሸማጋዮች፣ ታዛቢዎች ሊካተቱ እንደሚገባ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የህወሓት ውሳኔን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት በጉዳዩ ላይ መግለጫ አውጥቷል። የኀብረቱ ሊቀመንበር ሞሳፋኪ ማሀማት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት እና በኀብረቱ በኩል የሚደረግውን ድርድር እቀበላለሁ ማለቱን አድንቀዋል።
በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን ልዩ እድል ነው ብለዋል። የፌደራል መንግሥቱ ቀድሞውኑ በኀብረቱ ይደረግ ሲል የነበረውን ድርድር በተመሳሳይ የህውሓት ቡድን እቀበላለሁ ማለቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ኹለቱም አካላት አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉና በቀጥታ ወደ ውይይት እንዲያመሩ አሳስበዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አሜሪካ የኢትዮጵያን አዲስ አመት አስመልክቶ ባወጣችው መግለጫ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፈል በሚደረግው ጦርነት ኤርትራ እና ሌሎች ኃይሎች ግጭቱማ ከማባባስ እንዲቆጠቡ አሳባለች።
በተጨማሪ የአፍሪካ ኀብረት የፌደራል መንግሥትና የህወሓት ቡድን ጦርነቱን አቁመው በተቻለ መጠን ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲመጡ እያደረገ ያለውን ጥረት የሚያስመሰግን ነው ብላለች።
ግጭቱን በሰላም ለመፍታት የሚደረገውን ሂደት ለመደገፍ ዝግጁ መኾኗን በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶኒዮ ብሊንከን በኩል አስታውቃለች።
ለስድስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. እንደና ማገርሸቱ የሚታወስ ነው።
በሙሉጌታ በላይ
2022-09-12
