ሀገሬ ቲቪ

የሀገራችን የዘውድ ስርዓት ማብቂያ

ኢትዮጵያ በዘውዳዊ ስርዓት ለረጅም ዘመን ስትመራ ቆይታለች። ይሄው ዘመናትን የተሻገረው ጥንታዊ ስርዓት ግን ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኋላ መሻገር አልቻለም። በጊዜው የነበሩ የህዝብ እና የወታደሩ ጥያቄዎች ደግሞ ወሳኝ ድርሻ ነበራቸው።

47 ዓመታትን መለስ ብለን 1967ን ስንቃኝ የዛሬዋ ዕለት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከስልጣናቸው የወረዱባት ዕለት ነበረች። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።

በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ይዞ የሚገኘው የሰሎሞን ስርዎ መንግስት ዘመናትን በአስተዳደር ዙፋኑ ላይ ቆይቷል። ምንም እንኳን በዛጉዌ ስርዎ መንግስት መቋረጥ ገጥሞት የነበረ ቢሆንም ዘውዱ እንደገና ቀጥሏል። ይሄው የአስተዳደር ስርዓት ዘመናትን ዘልቆ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር ደርሷል።

ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኋላ ግን ይቀጥል ዘንድ የሀገራችን ሁኔታ አልፈቀደለትም። የታሪካዊው የንጉሳዊ አስተዳደር ስርዓት ማብቂያም ከ47 ዓመታት በፊት ሆነ። የሰለሞናዊ ስርዎ መንግስት የመጨረሻው ንጉስ፣ በታላቅ ክብር ይታዩ የነበሩት እና በዓለም ስመ ጥር መሆን የቻሉት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ መስከረም 2/ 1967 ዓ.ም. የስልጣን ዘመናቸው እንዳበቃ ተነገራቸው።

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጨረሻ የስልጣን ዘመናት አመጽ የተጧጧፈባቸው ነበሩ። ገበሬው፣ ተማሪው፣ መምህሩ፣ ወታደሩ ሁሉም በየፊናው ተቃውሞ ላይ ነው። የወታደሩን ክፍል የደመወዝ እና ሌሎች ተጨማሪ ጥያቄዎች ለንጉሱ የሚያቀርቡ ተወካዮች የተሰባሰቡበት ኮሚቴ ደግሞ ደርግ በሚል ስም ተዋቅሯል።

ኋላም ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት የሚል አቋምን ይዟል። ከተማረውም ክፍል ድጋፍ ማግኘት ጀመሯል። ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ታማኝነቱን በተደጋጋሚ በመግለጥ ኮሚቴው ለንጉሱ በተደጋጋሚ ጥያቄውን እያቀረበ አቅሙን ማደርጀት፣ ተቀባይነቱን ማጠንከር ጀምሯል።

የፖለቲካዊ ጥያቄዎች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፊት ተቀባይነት እያገኙለት ነው። አካሄዱን ግን ታማኝነቱን በመግለጽ ላይ አድርጓል። ኋላም የተጽዕኖ ፈጣሪነቱ በዙፋኑ ፊት መታየት ጀመረ።

ኮሚቴው አቅሙን እያደረጀ መጥቶ 1966 ዓ.ም. አልፎ 1967 ዓ.ም. መጥቷል። የኢትዮጵያ ህዝብ በመስከረም 1/ 1967 ዓ.ም. የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓሉን አክብሮ በየቤቱ ከቷል።

ደርግ ደግሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ስልጣን መገዳደሩን ውስጥ ውስጡን ከማሳደጉ በተጨማሪ ጆናታን ዲንቢልቢ የተሰኘው የእንግሊዝ ጋዜጠኛ የቀረጸውን የተደበቀው ረሃብ የተሰኘውን የወሎን የጊዜው ረሃብን የሚያሳይ ፊልምን አሳይቶ ጃንሆይን ከህዝቡ መነጠል ፈልጓል።

ምንም እንኳን ይሄንን ረሃብ ንጉሱ ከዓለም ደብቀው ህዝብ አልቋል፤ የሚል አንድምታ ያለውን ፊልም ደርግ ቀደም ብሎ ያገኘው ቢሆንም ይበልጥ ንጉሱን የሚያስተች እንዲሆን የተወሰኑ ነገሮች በኢዲቲንግ እንዲጨመርበት አድርጓል። ፊልሙን ለማሳየት ምቹ ጊዜ ሲጠብቅም 1967 ዓ.ም. የዘመን መለወጫን መረጠ።

በዘመን መለወጫ ማምሻ ለህዝቡ ያ ዘግናኝ ፊልም በቴሌቪዥን ለህዝብ እንዲተላለፍ ተደረገ።በዚህ ሁሉ ከወታደሩ እና ፖሊስ ሰራዊት የተውጣጡ 109 አባላት ያሉት ኮሚቴ ደርግ የኃይለ ሥላሴን ስልጣን የመገዳደር ሂደት በጊዜው የሻለቃ መንግስቱ ኃይለ ማርያም ሚና ጉልህ ነበር።

አሳዛኙን የወሎን ረሃብ ፊልም በዘመን መለወጫ የተመለከተው የኢትዮጵያ ህዝብ በየቤቱ የቁጣ እንባ አነባ። የነበረው የጊዜው ለውጥ ፈላጊነት ጥያቄ ለንጉሱ ጥላቻ ታከለበት።

መስከረም 2/1967 ዓ.ም. ጠዋት ላይ በደርጉ ውስጥ የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆነው የተሰየሙት ሻለቃ ደበላ ዲንሳ ንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን መውረዳቸውን እንዲያረዷቸው የተመረጠውን አስራ ሶስት አባላት ያሉትን ቡድን እየመሩ ከቤተ መንግሥት ደርሰዋል፡፡ የደርግ አባላት ሌሊቱን የቤተመንግስቱ ጥበቃን ሲያጠናክሩ አድረዋል።

ከደርግ ተወክለው ለጃንሆይ መርዷቸውን ሊነግሩ ከሄዱት አባላት ሻምበል ደበላ ዲንሳ የኮሚቴውን የውሳኔ ቃል ለንጉሱ አነበቡ። የውሳኔው ቃል ጭብጥ ለሀገርና ህዝብ ደህንነት ሲባል ከስልጣን የወረዱ ሲሆን ለደህንነትዎ ሲባል ወደ ተዘጋጀልዎ ቦታ እንዲሄዱ ተወስኗል የሚል ነበር።

ቀስ በቀስ በኮሚቴው ስልጣናቸው የተገፋው ጃንሆይ ‘’ያላችሁትን በጥሞና አዳምጠናቹኃል። ለሀገር በጎ አስባችሁ ከተነሳችሁ የአገር ጥቅም ከራስ ጥቅም ማስቀደም አይቻልም።’’ ካሉ በኋላ የውሳኔውን ቃል ተቀብለናል አሉ።

ገና በጠዋቱ ከስልጣን ወርደዋል የሚለው ጥያቄ የተነበበላቸው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከአራት አስርት ዓመታት የስልጣን ቆይታ በኋላ ከቤተመንግስታቸው ተዘጋጀላቸው ከተባለው ስፍራ ውብ በሆነችው ሮልስ ሮይስ መኪናቸው ሳይሆን ባረጀችዋ ቮልስ ዋገን መኪና ተጭነው ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ተወሰዱ፡፡

የሰለሞናዊ ስርዎ መንግስት ማብቂያ፣ የሶሻሊስት ኢትዮጵያም መጀመሪያ ሆነ።

በአብርሃም በለጠ
2022-09-12