የስፖርቱ ዓለም መዝናኛ ብቻ አይደለም። በርካታ አስደንጋጭ እና አሳዣኝ አጋጣሚዎች በውስጡ ተመልክተንበታል።
በርካቶች በዚህ ሜዳ ላይ ለመጫወት የገቡ ነበሩ ተብለዋል፤ የሚወዱትን ክለባቸውን እና ሀገራቸውን ለመደገፍም በስታዲየም የታደሙ ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል።
እነዚህ የሰላማዊ ጦርነት ሜዳዎች የሀዘን ድባብም ያላጡ ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን በዚህ ሜዳ ውስጥ ከጨዋታው ባለፈ አንዱ ለአንደኛው መድሃኒት ነው።
መረዳዳት፤ መደጋገፍም የስፖርቱ ዓለም መለያም ጭምር ነውና። ዛሬ የመረጥነው ታሪክም የዚህ የመደጋገፍ አንዱ አካል ነው።
ነገሩ ከትላንት በስቲያ በስፔን የላሊጋ ውድድር ጨዋታ ላይ የሆነ ነው። በሜዳውስጥ ባርሴሎና ካዲዝን እየገጠመ ነው፤ ባርሴሎና ጨዋታውን 2 ለምንም እየመራ በነበረበት ሰዓት፤ አንድ ደጋፊ በተመልካች ቦታ ላይ እያለ እራሱን ይስትና ይወድቃል።
ጨዋታው ቆመ ወዲያውኑ የሀኪሞች ቡድን እርዳታ ለማድረግ በቦታው ላይ ሲገኙ፤ የተመሪው ቡድን ግብ ጠባቂ ጀርሚስ ሌስማም እየሮጠ የመጀመሪያ እርዳታ መስጫ ሳጥን በእጁ ይዞ ለህክምና ቡድኑ አቀበላቸው።
ነገሩ የበርካቶችን ልብ ያሞቀ ነበር፤ እንዲህ ያሉ መደጋገፎች ሁሉም ቦታላይ ሊኖሩ ይገባልም አሰኝተዋል። ጨዋታው በዚሁ አጋጣሚ ሳቢያ 10 ለሚጠጉ ደቂቃዎች ተቋርጧል።
ደጋፊውም የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና እርዳታ ከተደረገለት በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል። በቦታው ተጨማሪ እርዳታ መስጫ ያስፈልግ እንደነበር እናም ግብ ጠባቂው ትልቁን ኃላፊነት ተወጥቷል ሲሉ አንድ የህክምና ቡድኑ አባል ተናግረዋል።
ይህ ደጋፊ ወደ ሆስፒታል በሚወሰድበት ወቅት ሌላ ደጋፊ እንዲሁ እራሱን ስቶ ሲወድቅ በደህንነት ካሜራ እይታ ውስጥ ገብቷል። የደህንነት ካሜራ ተቆጣጣሪውም ለህክምና ቡድኑ በማሳወቅ።
በዚህም ተጨማሪ ጉዳቶች ሳይከተሉ የደጋፊውን ነፍስ መታደግ መቻሉን ሲኤን ኤን አስነብቧል። በቦታው ድጋፍ ላደረጉ ደጋፊዎች፣ ለጥበቃ ክፍሉ እና ምስጉን ተግባር ላደረገው ተጫዋች ምስጋና ተችሯቸዋል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-09-12
