ሀገሬ ቲቪ

የማኀበራዊ ልማት ቀረጥ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምን ይኾን?

የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመጠገን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እና ለማሻሻል ሲባል ይህ ታክስ መጣሉ በውይይ ወቅት ተገልጿል። ይህ ታክስ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ላይ የ 3 በመቶ እንዲከፈልባቸው ያስገድዳል።

እኛም ይህ ጉዳይ በባለሙያ ዐይን እንዴት ይታያል የሚለውን ጠይቀናል ይህ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ የቀረጡ መጠን የእቃው ዋጋ፣ ኢንሹራንስ እና የማጓጓዣ ወጪ ላይ ብቻ ተሰልቶ የሚጣል ስለኾነ ተጠቃሚው ላይ ያን ያህል የጎላ ተጸዕኖ እንደማያመጣ ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የፕሪሜር ኢንቨስትመንት ኮንሰልታንት ዳይሬክተር የኾኑት መላኩ ክ/ገብርኤል ነግረውናል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው በዚህ ደንብ ነፃ ከተደረጉት ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች በስተቀር በሁሉም ዕቃዎች ላይ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ የሚጣልና የሚሰበሰብ ይሆናል።

ከሱር ታክስ ነጻ የተደረጉ እንደ የኢንቨስትመንት ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ አውሮፕላን፣ የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወዘተ ያሉ ምርቶች አሁን ላይ 3 በመቶ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ተጥሎባቸዋል።

ይህ መውጣቱ አስፈላጊ አይደለም ያለውን የኑሮ ውድነት ያባብሳል ያሉን ደግሞ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የኾኑት አቶ ሸዋፈራው ሽታሁን ናቸው። የዚህን ቀረጥ ተፈጻሚነት ላይም ጥያቄ እንዳላቸው አቶ ሸዋፈራው አክለው ተናግረዋል።

የማኀበራዊ ልማት ቀረጥ አማካኝነት መንግሥት በዓመት 20 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ አለኝ ብሏል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-09-13