ሀገሬ ቲቪ

በሁለት እግሯ መራመድ የቻለችው ፓራላይዝዷ ሕፃን

አንዳንዴ እጅን በአፍ የሚያስጭኑ አስገራሚ ነገሮችን እንሰማለን፤ አሁን ልንነግራችሁ የወደድነውም ታሪክ እንዲሁ ነው። በርካቶችን ልባቸውን በሀዘንም በደስታም ሞልቶት ሰንብቷል።

ወላጆች ለልጆቻቸው የቱን ያህል ጥግ መሄድ እንዳለባቸው ማሳያም እየተደረገ ይሀኛል። እንዲህ ያለው መንፈሰ ጠንካራነት፤ ልብ ድረስ ዘልቆ የሚሰማ የልብ መሰበር፤ በእንባ ውስጥ የተሻለ ነገን አሻግሮ ማስተዋልን ይጠይቃል። ይህ ተስፋ ያለመቁረጥ እና የማመን ጥረት ውጤትም ነው።

ይህች የ8 ዓመት ሕፃን ስሟ አንቺ ይባላል፤ እንዲህ ቆማ መራመድ ከመቻሏ አስቀድሞ ሃኪሞች እስከ እድሜዋ ጀንበር ማብቂያ ድረስ በሚገፋ ዊልቸር ላይ ታሳልፋለች ያሏት ነበረች።

ዛሬ ግን እንደ ተተነበየላት አይደለችም፤ ጠንካራዋ ሕፃን የህይወትን ፈተና ገና በጨቅላነቷ ለመጋፈጥ ድፍረቱን አላጣችም ምስጋና ለቤተሰቦቿ ይሁን እና በ2013 ዓ.ም እንዲህ ሆነ አንቺ በቤት ውስጥ እየደነሰች በመጫወት ላይ ሳለች አደጋ ደረሰባት።

ወላጆቿ ፈጥነው ወደ ሀኪም ዘንድ ወሰዷት፤ ሀኪሞቹ ገና ዘላ፣ ቦርቃ ያልጠገበችው አንቺ ከባድ የአከርካሪ አጥንት (ስፓይናል ኮርድ) ጉዳት ደርሶባታል አሉ።

ያላት ተስፋም በሚፈፉ የተሽከርካሪ ወንበሮች ላይ ማሳለፍ እንደሆነ ለቤተሰቦቿ ተረዳቸው። የአንቺ ቤተሰቦች ግን ተስፋን አልቆረጡም ማድረግ ያለባቸው ሁሉ ለማድረግ ወሰኑ።

ወደ ቤታቸው ሲመለሰም ለልጃቸው የማገገሚያ ክፍለ ግዜን አወጡ። አንቺ ዳግም ለመራመድ አልታዘዝ ላለው ሰውነቷ የሚረዱ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀመረች።

በቀን ውስጥ ለ6 ሰዓታት ያህል አንቺ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ታሳልፋለች። ጠንካራዋ አንቺ ከ1 ወር ባልበለጠ ግዜ ውስጥ በሁለት እግሯ ለመቆም ችላለች።

በማገገሚያ ግዜያቶቿ ውስጥ ጡንቻዎቿን በምትታሽበት ግዜ በጣም ያማት እንደነበር ቤተሰቦቿ ይናገራሉ። የልጅ ህመም ምን ለወላጅ ያህል እንደሚያም የወለደ ያውቀዋል፤ የአንቺ ወላጆችም በእነዚያን ወቅቶች ልባቸውን ለሁለት የከፈለ፤ ተስፋን ያስቆረጠ ስሜት ውስጥ ይገባሉ።

እዚህ ጋር በቃን ከዚህ በኋላ የልጃችንን ስቃይ ማየት የለብንም አምላክ እንዳደረገ ያድርጋት እስከማለት ደርሰውም ነበር። ሁሉም ግን ለአንቺ ነገ ነውና ስቃዩአን እና መከራዋን ያለመታከት ችለውታል።

ከዚያ ሁሉ መከራ እና ስቃይ በኋ ግን ሀኪሞቹ ብለው የነበረውን ሀሰት ነው አሰኝታለች፤ አሁን እንደመሰሎቿ እንዳሻት የምትቦርቅ ሆናለች።

በሳምሶን ገድሉ
2022-09-13