ሀገሬ ቲቪ

ቀዳሚው የእስራኤል ፍልስጤም የሰላም ስምምነት

እስራኤል እና ፍልስጥኤም ከአስርት አመታት ደም መፋሰስ በኋላ የሀገራቱ ተወካዮች በአሜሪካ ነጩ ቤተ መንግስት ያዘጋጀውን የሰላም መግባቢያ ተፈራርመዋል። ይሄንንው መፈራረም ሀገራቱ ያደረጉት በዛሬዋ ዕለት በ1986 ዓ.ም. ነበር።

የመርሆች ድንጋጌ (Declaration of Principles) የተሰኘው ስምምነታቸው ሰላም ለማድረግ እና የግጭት ስፍራዎችን ለመጋራት የተስማሙበት የመጀመሪያው ስምምነታቸው ነው። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።

በፍልስጤም የአይሁዶች እና የአረቦች ግጭት መጀመር ወደ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ መለስ ይላል። በጊዜው በቀጠናው እንግሊዝ ቁጥጥር ነበራት።

ራሳቸውን ጽዮናውያን ሲሉ የሰየሙት እና ተበታትነው ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች ደግሞ ከአውሮፓ እና ሩስያ ተሰደው የአይሁዶች ጥንታዊ ግዛት ብለው ወደሚጠሩት ስፍራ መጥተው የአይሁዶች ብሄራዊ ሀገርን መመስረት ፈለጉ።

በስፍራው ማለትም በፍልስጤም የነበሩ አረቦች ደግሞ የአይሁድን ስደተኞች ለመግታት የፍልስጥኤም ግዛትን ለመመስረት መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

ይሁንና ግን በ1940 ዓ.ም. እስራኤል እንደሀገር መመስረቷን አሳወቀች። አምስት የአረብ ሀገራት ፍልጥኤማዊ አረቦችን በመደገፍ እስራኤልን አጠቁ። እስራኤል በሀገራቱ ላይ ድልን ተቀዳጀች ።

ለፍልስጥኤማውያን እስራኤል ከመመስረቷ አስቀድሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተወሰነላቸውን ክልል ሳይቀር ያዘች። በተባበሩት መንግስታት አስገዳጅነት እስራኤል ከግብጽ፣ ሌባኖን፣ ጆርዳን እና ሶርያ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት አደረገች።

የተኩስ አቁሙ እስራኤል በጦርነቱ የያዘቻቸውን ግዛቶች ይዛ እንድትቀጥል በር ከፈተ። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አረቦች ከስፍራዎቹ እንዲለቁ ያሉትም መብታቸው እንዲገደብ ተደረገ።

በተደጋጋሚ እስራኤል ከአረብ ሀገራቱ የገጠሟት የተቃውሞ ጦርነቶችም አልበገሯትም። ይባስ ብሎም ግዛቶቿን እንድታሰፋ ምክንያት ሆኗት። ያም ሆኖ ግን በፍልስጥኤም ምድር የእስራኤል ተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል።

ከ1959ኙ የስድስቱ ቀን ጦርነት በኋላ በፍልስጥኤም የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት (PLO) እንደፍልስጥኤም የነጻነት እንቅስቃሴ ተደርጎ መቆጠር ጀመሯል።

ይሄው ቡድን በ1950ዎቹ አጋማሽ ተመስርቶ በውጭ ያሉ የፍልስጥኤማውያን አረቦች የተለያዩ ቡድኖች የፖለቲካ መጠለያ ሆኗል። ለእስራኤል መጥፋት እና ለፍልስጤም ሀገርነት መመስረት ጥሪ አድርጎ ነበር።

የቡድኑ መሪ ያሲር አረፋት በእስራኤል ላይ የደፈጣ ጥቃትን ጆርዳን ኋላም ከሌባኖን ጀምረዋል። የሽብር ጥቃትንም በእስራኤላውያን ላይ አጧጡፈዋል። ያሲር አረፋት በ1970ዎቹ መጀመሪያ እንደፍልስጥኤማውያን ተወካይ አለም አቀፍ እውቅና አግኝተዋል።

የግብጽ እና ሶሪያ ኃይሎች በስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽመው በ1965 ዓ.ም. ሶስተኛው የአረብ እስራኤል ጦርነት ከተካሄደ በኋላ የግብጹ ሳዳት እና የእስራኤሉ ሜናቼም ቤጊን የካምፕ ዴቪድ ስምምነትን ተፈራረሙ።

ይሄው የመጀመሪያው የእስራኤል እና የአረብ ሀገር የሰላም ስምምነት የሀገራቱ መሪዎች የኖቤል ሽልማትን እንዲጋሩ አድርጓል። በርግጥ ስምምነቱ የግብጹ ሳዳት በጽንፈኞች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል።

በ1970ዎቹ ፍልስጥኤማውያን ከአይሁድ ሰፋሪዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገቡ። የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት PLO)ን ለማፍረስም እስራኤል ሌባኖስን አጠቃች።

በ1980ዎቹ መጀመሪያ በጋዛ እና ዌስት ባንክ የነበሩ የፍልስጥኤም ነዋሪዎች በስራኤል ባለስልጣናት ላይ ኢንቲፋዳ የተሰኘ ከፈተኛ ተቃውሞን ጀመሩ። የጆርዳን ንጉስ በዌስት ባንክ ያለውን አስተዳደራዊ ኃላፊነት ሲወስዱም በስፍራው የፒኤልኦ ተጽዕኖ ከፍ አለ።

ተቃውሞው በተጧጧፈበት ያሲር አረፋት ነጻ የፍልስጥኤም ግዛትን በጋዛ እና ዌስት ባንክ አወጁ። ቀጥለውም የእስራኤልን የመኖር መብት እውቅና ሰጥተው ለሰላም ስምምነት ፈቃደኝነታቸውን ማሳየት ጀመሩ። እስራኤል ግን ከፒኤልኦ ጋር ቀጥተኛ ንግግር ለማድረግ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች።

በአሜሪካ በነጩ ቤተ መንግስት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሺሞን ፔሬዝ እና የፍልስጥኤም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ የሆኑት ማህሙድ አባስ የመርሆች ድንጋጌ (Declaration of Principles) የተሰኘውን ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ የእስራኤል ጦር ከጋዛ እና ዌስት ባንክ እንዲወጣ ብሎም በአብዛኛው የዌስት ባንክ ክፍል ቀስ በቀስ ስልጣኑ ከፍ የሚል የፍልስጥኤም አስተዳደር እንዲቋቋም የሚጠይቅ ነበር።

ለዚህ የሰላም ስምምነታቸውም በ1987 ዓ.ም. ያሲር አረፋት፣ ይስሃቅ ረቢን እና ሺሞን ፔሬዝ የኖቤል ሽልማትን በጋራ አግኝተዋል።

ምንም እንኳን በ1988 ዓ.ም. ይስሃቅ ረቢን በአይሁድ አክራሪ ከተገደሉ በኋላ የሰላም ሂደቱ በሺሞን ፔሬዝም ዘመን ቢቀጥልም ከዚያ በኋላ ግን የሰላም ሂደቱ ተስተጓጉሏል።

ይሄው በዛሬዋ ዕለት ያደረጉት ስምምነት የመጀመሪያው የሰላም ስምምነታቸው ተደርጎ ተመዝግቧል።

በአብርሃም በለጠ
2022-09-13