ሀገሬ ቲቪ

በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት

ደቡብ አፍሪካ ህጋዊነትን በተላበሰው የአፓርታይድ የዘር መድሎ ስርዓት ተፈትናለች። በብዙ ትግልም የአፓርታይድ ስርዓት ተወግዷል። ሂደቱ ግን ብዙ ፈተናዎችን ያስተናገደ ነበር። ሀገሪቱን ከአፓርታይድ ስርዓት በማውጣት ሂደቱ ግጭቶችን በማስቀረት በኩል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሰላም ስምምነት የተደረገው በዛሬዋ ዕለት በ1984 ዓ.ም. ነበር። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።

ጊዜው 1984 ዓ.ም. ነው። ደቡብ አፍሪካ የተጫናትን የአፓርታይድ ስርዓት ለማስወገድ በሂደት ላይ ናት። ስርዓቱን ማስወገዱ ግን ግጭት የታጣበት አልነበረም።

በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ የጊዜው የደቡብ አፍሪካ መንግስት፣ የነኔልሰን ማንዴላ ፓርቲ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ እና ኢንካታ ፍሪደም ፓርቲ በጋራ ያደረጉት የሰላም ስምምነት የራሱን አስተዋጽኦ ግጭቶችን በማስወገድ በኩል አበርክቷል።

አፓርታይድ ይሉት ቃል በደቡብ አፍሪካ ምድር መለያየት የሚል ትርጉም ያለው የስርዓት መጠሪያ ነው። ይሄው በህግ የተደገፈ የቆዳ ቀለምን መሰረት ያደረገ መነጣጠል ነጭ ባልሆኑ ጥቁር አፍሪካውያን ላይ የተጫነ ቀንበር ነበር።

በዚህ ስርዓት አብዛኛው ቁጥርን የሚሸፍነው ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ ህዝብ ከነጮች ተነጥሎ እንዲኖር፣ ከነጮች የተለየ አገልግሎት እንዲወስድም ይገደድ ነበር።

በርግጥ የነጭን የበላይነት የሚያቀነቅነው ስርዓት በደቡብ አፍሪካ ህግ የሆነው በ1940ዎቹ መጀመሪያ ነው። አፓርታይድ ህግ ሲሆን የነጭ እና ደቡብ ጥቁር አፍሪካውያንን ጋብቻ እና የፍቅር ግንኙነት አጥብቆ ከለከለ።

ነጮችን ከሁሉም የበላይ አደረገ፤ ጥቁሮችን ደግሞ በመጨረሻው ድልድሉ። ከዚያ በፊትም ቢሆን ደቡብ አፍሪካ ነጻነቷን ካገኘች በኋላም የዘረኝነት ዕሳቤው ቀደም ብሎም የነበረ ነው።

አፍሪካነር ናሽናል ፓርቲ አፓርታይድ በሚል መፈክሩ ጠቅላላ ምርጫውን አሸንፎ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ነበር ስርዓቱን ህጋዊ ያደረገው። የአፓርታይድ ስርዓት ጥቁሮችን እና ኤስያውያንን ከነጮች መለየት ብቻ ሳይሆን ጥቁሮችን በጎሳ ርስ በርስ የመነጣጠል ዓላማን ያነገበም ነበር።

በአፓርታይድ ህግ መሰረተ 80 በመቶው የሀገሪቱ መሬት ለጥቂት ነጮች ንብረት ሆነ። መከፋፈሉን ለማጥበቅ እና ግንኙነትን ለማስቀረትም ነጮች የሚገለገሉባቸውን ተቋማት ለብቻቸው ተለየ።

ነጭ ያልሆኑ የጉልበት ሠራተኞች ማኅበራት እንቅስቃሴ እንዲገደብ ና ነጭ ያልሆኑ ሰዎች በብሔራዊ መንግሥት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይሳተፉ ተከለከለ።

ስርዓቱ ያልጣማቸው ደቡብ አፍሪካውያን ግን በተለያየ መንገድ ሁነቱን መቃወማቸው አልቀረም። የአፓርታይድ ስራዓትን ለማስቀረት ከሰላማዊ ትግል እስከ ትጥቅ ትግል ተጉዘዋል።

ከእነዚህ ቡድኖች ደግሞ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ፣ ሳውዝ ኢንድያን ናሽናል ኮንግረስ እና ፓን አፍሪካን ኮንግረስ ይጠቀሳሉ። በተቃውሞዎች ውስጥም ብዙዎች በደቡብ አፍሪካ የጊዜው መንግስት በጅምላ ተገድለዋል። ታስረዋል። ተሰቃይተዋል።

የአፓርታይድ ስርዓትን በህግነቱ አጽንቶ መቆየት የፈለገው የደቡብ አፍሪካ መንግስት ላይ የበረቱት ውስጣዊ ሰላማዊም የትጥቅም ትግሎች ብሎም አለም አቀፋዊ ጫናዎች አፓርታይድን በህግነቱ እንዳይቀጥል ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ከልክለውታል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፓርታይድ ስርዓትን ያወገዘው በ1960ዎቹ አጋማሽ ነበር። የጦር መሳሪያ ግዥ ማዕቀብንም በደቡብ አፍሪካ ላይ ጥሏል።

አሜሪካ እና እንግሊዝም ቢሆኑ ሀገሪቱ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የጣሉት በ1970ዎቹ መጨረሻ ነበር። ጫናዎቹ የናሽናል ፓርቲ መንግስት መሪ የሆኑት ፔተር ቦታ ማሻሻያዎችን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።

ደ ክለርክም ቢሆኑ በአፓርታይድ ተቃውሟቸው ለ27 ዓመታት በእስር ያሳለፉትን ኔልሰን ማንዴላን በ1982 ዓ.ም. ከእስር ለቀዋል። ደቡብ አፍሪካ በመጨረሻም አዲስ ህገ መንግስትን ለማስደቅ ድርድር ውስጥ ገብታለች።

ሀገሪቱን ከአፓርታይድ ስርዓት አውጥቶ ወደ ዴሞክራሲ የመምራት ድርድሮቹ ግን ግጭቶች አላጡትም። የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመንግስት ድርድር በተጧጧፈበት በ1980ዎቹ መጀመሪያ የስልጣን ሽኩቻዎቹ እና የፖለቲካ ግጭቶች መጨመር ጀምረዋል።

ለዚህም ሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚገዛ ስምምነት አስፈልጓታል። በግጭቱ ስጋት ያደረባቸው ደቡብ አፍሪካውያን በዴ ክለርክ ናሽናል ፓርቲ ንላይ እምነት አላሳደሩም። እዚህ ላይ ነው የብሄራዊ ሰላም ስምምነት (NPA) የሚመጣው።

ይሄንን ስጋት ለመቀነስ የሃይማኖት ተቋማት ተነሳሽነቱን ወሰዱ። የቤተክርስቲያን መሪዎች ለድርድሩ ሰላማዊነት ለስምምነት ሲቀሰቅሱ የቢዝነስ መሪዎችም ተቀላቀሏቸው።

በቤተክርስቲያን መሪዎች እና ሁኔታዎች ግፊት በ1983 ዓ.ም. ፓርትዎች ንግግር ማድረግ ጀመሩ። የብሄራዊ የሰላም ስምምነቱንም (NPA)ን በዛሬዋ ዕለት በ1984 ዓ.ም ተፈራርመዋል።

ደቡብ አፍሪካም በድርድሮች ከአፓርታይድ ወደ ሁሉን አካታች ምርጫ መምጣት ችላለች። ስምምነቱ ግን ግጭቶችን በማስወገዱ ረገድ አስተዋጽኦን አበርክቷል።

በአብርሃም በለጠ
2022-09-14