ሀገሬ ቲቪ

የዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ በጣም አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል

ከዓለማችን ህዝብ ግማሽ ያህሉ ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚከሰቱ አደጋዎች ተጋላጭ እንደሆነ ይቆጠራል። ጎርፍ፣ ከፍተኛ ሙቀት፣ ድርቅ፣ ሰደድ እሳትና አውሎ ነፋስ ደግሞ በዚሁ ምክን ያት የሚከሰቱ አደጋዎች ናቸው።

አሁንም ታዲያ የአየር ንብረት ለውጥ በርካታ ሀገራት ላይ የጥፋት በትሩን እያሳረፈ መኾኑን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ተቋማት የምርምር ውጤታቸውን ሪፖርት ባደረጉበት ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጎተሬዝ ጉዳዩ አሁን ላይ በዋዛ የሚታይ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

የቀረቡ ሪፖርቶችን በበላይነት ሲመራ የነበረው ዓለም አቀፉ የሚትሮሎጂ ድርጅት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ዓለም ወደተሳሳተ አቅጣጫ እየነጎደች ነው ሲል አሳስቧል።

የግሪንሃውስ ጋዝ መጠን ወይም አየር በካይ ጋዞች በከባቢ አየር ውስጥ እየጨመረ እንደኾነ ተሰምቷል። በተለይም የሀገራት መሪዎች ኢንዱስትሪዎች የሚለቁትን በካይ አየር ለመቀነስ እና የዓለም የሙቀት መጠን የኢንዱስትሪ ዘመን ከነበረበት ከ 1.5 ድግሪ ሴልሺየስ ለማውረድ ከወረቀት ስምምነት ያለፈ የተግባር ሥራ አለመሥራታቸው ምድር ወደ አደገኛው የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ እንድትቃረብ እየገፋ ነው ተብሏል። አሁንም ቢኾን በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የሚከሰቱት አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ ነው።

አንቶኒዮ ጎተሬዝ በቅርቡ በፓኪስታን ከ1400 በላይ ሰዎች የሞቱበት መጠነ ሰፊ የጎርፍ አደጋ እና በአውሮፓ ዜጎችን እየፈተነ ያለው ከፍተኛ የሙቀት ማዕበልን እንደአብነት በማንሳት እነዚህ ችግሮች ተፈጥሮ ያመጣቸው ሳይኾኑ በአየር ንብረት ለውጡ የተከሰቱ ናቸው ብለዋል።

እንደ ነዳጅ የተፈጥሮ ጋዝ የድንጋይ ከሰል ያሉ የተፈጥሮ የሀይል ምንጮችን ነጻ የማድረጉ ሥርዓት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። ምክን ያታቸውን ሲያብራሩም ለቋሚ ችግር እና ቀውስ የዳረገ መመሪያ ነው በማለት አጣጥለውታል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዚህ ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጣው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን በ2012 ዓ.ም በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር 1.2 በመቶ ከፍ ብሏል። ያለፉት ሰባት ዓመታት ደግሞ በታሪክ ከተመዘገቡት ሁሉ እጅግ በጣም ሞቃታማ ነበሩ።

የምድር አማካይ የሙቀት መጠን ኢንዱስትሪ ከተስፋፋበት ዘመን በፊት ከነበረው አማካይ የሙቀት መጠን 1.1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ ብሏል። የዘርፉ ሊቃውንት እስከ 2026 ዓመታዊው አማካይ ሙቀት ከ1ነጥብ1 ድግሪ ሴልሺየስ እስከ 1.7 ሴልሺየስ ሊደርስ ሊደርስ ይችላል ማለታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል። ይህም ማለት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ 1.5 ድግሪ የሙቀት መጠንን ማለፍ የምንችልበት ዕድል አለ ማለት ነው።

ምን አልባትም አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ በዚህ ክ/ዘመን መጨረሻ 2.8 ድግሪ ሴልሺየስ ሊደርስ እንደሚችል ነው የተተነበየው በተጨማሪ በ2050ዎቹ ከ1.6 ቢሊዮን የሚበልጡ የከተማ ነዋሪዎች ቢያንስ ቢያንስ 35 ሴንቲ ግሬድ በሚሆን አማካይ የሙቀት መጠን ኑሮአቸውን ሊገፉ ይችላሉ።

በወንድምአገኝ አበበ
2022-09-14