የገቢዎች ሚኒስቴር ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አልሰበሰብኩም አለ፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር በ2014 በጀት ዓመት 360 ቢሊየን ብር የመሰብሰብ እቅድን አስቀምጦ ሥራ ጀምሯል፡ ባሳለፍናቸው አምስት የበጀት ዓመቱ ወራት 158 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 147 ነጥብ 3 ቢሊየን ወይንም የእቅዱን 92 ነጥብ 6 በመቶ አሳክቷል፡፡ በገቢዎች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ኡሚ አባጀማል የገቢ አፈጻጸሙን አስመልክቶ እንደገለጹት ገቢ አሰባሰቡ በሀገራችን በተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ እና የኮቪድ ወረርሽኝ ችግር ውስጥ በመሆን የተመዘገበ ነው ብለዋል፡፡ በአምስቱ ወራት በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት በመቀሌ ገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮምሽን ቅርንጫፎች በድምሩ 1ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም ምንም ገቢ አልተሰበሰበም ፡፡ በተመሳሳይ በኮምቦልቻ ገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮምሽን ቅርንጫፎች 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 1ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ብቻ ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ በዚህም ከመቀሌ እና ኮምቦልቻ አራት ቅርንጫፎች ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ውስጥ 1ነጥብ 9 ቢሊየን ብቻ ሲሰበሰብ ቀሪው 2.3 ቢሊየን ብር ሳይሰበሰብ መቅረቱን ዳይሬክተሯ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሯ ጦርነቱ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው ጫና በገቢው ዘርፍም ተስተውሏል ብለዋል፡፡ በተለይ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ የኮምቦልቻ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እና የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሙሉ በሙሉ በጦርነቱ ወድሟል ፡፡ በቀጣይም ሰላም በተመለሰባቸው ቅርንጫፎች በፍጥነት ወደተግባር በመግባት በገቢው ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ጥረት እንደሚደረግ ተነግሯል፡፡
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-29
