ቻይና ራሷን እንደቻለች ሀገር አልቆጥራትም በክፉ ቀን ከአካሌ የተነጠለች ናት ስትል ታይዋንን ወደ ራሷ ግዝት ለመጠቅለል ጫፍ ላይ ስለመድረሷ ይወራል። ከወራት በፊት የቻይና የጦር ጀቶች ወደ ታይዋን የአየር ክልል መግባታቸው ለዚሁ ፍላጎቷ አንድ ማሳያ ኾኖ ይነሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ለታይዋን ጠበቃ በመቆም ለቻይና ብዙ ማሳሰቢያዎችን ስጸጥ ቆይታለች ዛሬም ታዲያ የአሜሪካ ጦር ታይዋንን ከቻይና ወረራ እንደሚከላከሉ አስታውቀዋል።
አሜሪካ ለዩክሬን እንዳደረገችው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ብቻ ለታይዋን እንደማታደርግ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አረጋግጠዋል። ቻይና ታይዋንን ከወረረች ወታደሮቻችን ከታይዋን ጎን ቆመው ከቻይና ጋር ይዋጋሉ ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በጃፓን ቶኮዮ ተገኝተው የነበሩት ባይደን ቻይና አንዳች ወታደራዊ እርምጃ የምትወስድ ከኾነ አሜሪካ ቆማ አትመለከትም ማለታቸውን ሲኤንኤን በዘገባው አስታውሷል።
ጆ ባይደን ከሲቢኤስ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ አሁንም በድጋሜ ይህን አረጋግጠዋል።
“የአንድ ቻይና ፖሊሲ አለ ታይዋን ነጻነቷን የተመለከተ የራሷን ውሳኔ ማድረግ ትችላለች። ታይዋን ነጻ ሀገር እንድትኾን አንገፋትም፤አናበረታታም ይህ የራሳቸው ውሳኔ ነው”
የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎ አሜሪካ በጉዳዩ ላይ ያላትን ስትራቴጂካዊ “አሻሚነት” የተሰኘውን ፖሊሲ ለታይዋን ነጻ ሀገር ስለመሆኗ እንውቅና በመስጠት ፖሊሲዋን እየለወጠች ነው የሚሉ ጥርጣሬዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተወረወሩ ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ የነጩ ቤተመንግሥት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ በፍጹም የፖሊሲ ለውጥ አልተደረግም አሜሪካ በታይዋን ላይ ያላት አቋም እንደቀድሞ በስትራቴጂካዊ “አሻሚነት” የምትመለከተው ነው ሲል አስታውቋል።
ባለፈው ሐምሌ ወር የአሜሪከ አፈ-ጉባኤ ናንሴ ፔሎሲ ታይዋንን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ቻይና አሜሪካ የበለጠ የጎሪጥ እንዲተያዩ ኾነዋል።
አሁን ላይም ይህ የጎሪጥ መተያየታቸው የበለጠ የከረረ ይመስላል በተለይም በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አሜሪካ ለታይዋን 1.1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎች እና ፀረ ሚሳኤሎች ለመሸጥ ከተስማማች በኋላ በድርጊቱ ቻይና ክፉኛ መቆጣቷ ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቻይና ሥጋት ያደረባት በአሜሪካ ጥብቅና ድፍረትን ያገኘች የምትመስለው ደሴቷ ታይዋን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ደርሶባታል።
በደቡብ ምሥራቅ ታይዋን በሬክተር ስኬል 6.9 በተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ሕንጻዎች መውደማቸው ተሰምቷል ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ በ140 በላይ በሚኾኑ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-09-19
