ሀገሬ ቲቪ

የውጪ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ዕድል እና ሥጋት

ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በሯን ለውጪ ባንኮች ዘግታ ቆይታለች ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. 13ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያደረገው የሚኒስትሮች ም/ቤት ግን የውጪ ባንኮች የሀገር ውስጥ ገበያን እንዲቀላቀሉ የሚፈቅድ ፖሊሲ አጽድቋል።

ውሳኔው ጥሩ እርምጃ እንደሆነ ከጣቢያችን ጋር ቆያታ ያደረጉ የፋይናንስ እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተናግረዋል። ለብሔራዊ ባንክም ሆነ ለሀገር ውስጥ ባንኮች ሰፊ ዝግጅት የሚጠይቅ ውሳኔ እንደኾነ የፋይናንስ እና ማኔጅመንት አማካሪ የሆኑት አቶ አንተነህ ሰብስቤ ተናግረዋል።

የውጪ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ከሀገሪቱ ባንኮች ብድር ለማግኘት ያለውን ውጣ ውረድ እንደሚያስቀርና ባንኮች የሚጥሉትን ከፍተኛ የብድር ወለድ እንዲያስተካክሉ ያስገድዳቸዋል ያሉን ደግሞ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ናቸው።

በተጨማሪም አቶ ሸዋፈራሁ የነገሩን ፖሊሲው መጽደቁ አለም ዓቀፍ መመሪያ የማይከተለውን የሀገራችንን የባንክ ምስረታ ሥርዓት ሊያሲዘው እንደሚችል ነው።

እነዚህ የውጪ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ዘርፉን በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ በቂ የፋይናንስ እና የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲኖር፤ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለማምጣት የውጪ ባንኮች ወደ ሀገር መግባታቸው ጥቅም ይኖረዋል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈ ግን እንዚህን ባንኮች በሚገባ መቆጣጠር የሚያስችል ፖሊሲ ካልተዘጋጀ ሊኖረው ስለሚችለው ጉዳት አቶ አንተንህ ይህንን ነግረውናል።

በኢትዮጵያ ያሉ ባንኮች ተወዳዳሪ እና ብቁ መኾን እንዲችሉ ከወዲሁ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-09-20