የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ ነው። በዩክሬይን ሰማይ ስር ተጀምሮ ምዕራባውያኑን ከሩስያ በተቃራኒ ያቆመው የዩክሬይን ጦርነት ደግሞ 205 ቀናትን አልፎ ዛሬም እንደቀጠለ ነው።
በዚህ ሳምንት በሚከናወነው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይም ይሄው ጦርነት ምዕራባውያኑ እና ሩስያ ደጋፊዎችን ከጎናቸው ለማሰለፍ በፉክክር የሚታትሩበት ይሆናል ተብሎ ተጠብቋል።
በ77ተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መሪዎች ከዩክሬይን ጦርነት በተጨማሪም ስለረሃብ ስጋት እና አለም አቀፉ የአየር ንብረት ቀውስ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ምድር የታየ ትልቁ ጦርነት ነው የሚባልለት የዩክሬይን ጦርነት አሜሪካ እና አጋሮቿ ከሩስያ በተቃራኒው ዛሬም በጠቅላላ ጉባኤው ይቆማሉ እየተባለ ነው። ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህም ቢሆን ሃያላኑን ያፋጠጠው ጦርነት ዓለም አቀፍ የምግብ ብሎም የሃይል ቀውስ ያስከተለ መሆኑም የሚታወቅ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የመጡትን የጎርፍ እና የረሃብ አደጋዎች ለመከላከል መረባረብ አለብን ሲሉ የተደመጡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የሆኑት አንቶንዮ ጉተሬዝም ለጠቅላላ ጉባኤው ሲናገሩ ዓለም በትልቅ ስጋት ላይ ናት ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“ጠቅላላ ጉባዔው በታላቅ የስጋት ጊዜ የሚካሄድ ስብሰባ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ከኖሩት የጂኦስትራቴጂክ ክፍፍሎች ሁሉ ትልቁ ላይ ነን ። መከፋፈሎቹ ላጋጠሙን ዓለም አቀፋዊ ችግሮች የጋራ ምላሽ ለመስጠት እንዳንችልም አስረውናል።” አንቶንዮ ጉተሬዝ
የዚሁ ትልልቅ ዓለም አቀፋዊ ክፍፍል ምንጭም የሩስያ ዩክሬይን ጦርነት ነው ሲሉ ዋና ጸሃፊው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ከሶስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገናኝተው የሚመክሩት መሪዎች ግጭቶችን፣ የዓየር ንብረት ቀውስን እና በሃያላኑ መካከል ያደገውን መከፋፈል መፍታት እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል።
ይሄው በመካሄድ ላይ ያለው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አሜሪካ እና አጋሮቿ ባንድ ጎራ ሩስያ ደግሞ በሌላ ጎራ በሩስያ ዩክሬይን ጦርነት ላይ ደጋፊ ለማሰባሰብ የሚያደርጉት ፉክክር መድረኩ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል እየተጠቆመ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በረሃብ እና የአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተኑ ያሉ ሃገራት ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው እንዳይሸፋፈን ለማድረግ ይጥሩበታል ተብሎ ይጠበቃል።
አንቶንዮ ጉተሬዝ 80 በመቶውን የአየር ብክለት ድርሻ ያደጉ ሃገራት ይወስዳሉ፤ የአየር ንብረት ቀውስን ለመቀነስም መረባረብ አለብን ብለዋል።
በንግስት ኤልሳቤጥ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ የታደሙ እና የዲፕሎማሲ ስራዎችንም ጎን ለጎን በማካሄድ ላይ የነበሩት መሪዎች ከለንደን ወደ ኒውዮርክ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ለመምከርም አምርተዋል።
በአብርሃም በለጠ
2022-09-20
