የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት 1 ሺሕ የሚጠጉ ፍልሰተኞችን ከሞት ታድጌያለሁ አለ፡፡ አይ.ኦ.ኤም በባለፈው ሳምንት ብቻ ነው በሊቢያ የባህር ዳርቻ ያሉ ፍልሰተኞችን የታደገው፡፡ ሊቢያ የሜዲትራንያንን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ለሚፈልጉ ፍልሰተኞች ተመራጭ የመነሻ ሀገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ፍልሰተኞቹ ከሊቢያ የባህር ዳርቻ ተይዘው ወደ ሊቢያ እንደተመለሱ ተቋሙ ተናግሯል፡፡ ከፈረንጆቹ ታህሳስ 19 እስከ 25 ባለው ጊዜ ውስጥ 969 ፍልሰተኞች ታድነው ወደ ሊቢያ መመለሳቸዉን ሲጂቲኤን ጽፏል፡፡ በአንድ አመት ብቻ በድምሩ 32 ሺህ 425 ህጋዊ ማስረጃ የሌላቸው ፍልሰተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው፣573 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋችው እንዲሁም 933 ፍልሰተኞች ከሊቢያ ባህር ዳርቻ በማዕከላዊ ሜዲትራኒያን መንገድ መጥፋታቸውን ድርጅቱ ገልጿል። እንደፈረንጆቹ በ2011 የሊቢያው ሟቹ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ከወደቁ በኋላ ሀገሪቱ ከነበረችበት አለመረጋጋት እና የፀጥታ ሁኔታ አንፃር፤በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ የባህር ዳርቻዎች ለመዝለቅ ሊቢያን ሲመርጡ ይስተዋላል። ይህም የሰሜን አፍሪካዊቷን ሀገር የሜዲትራንያንን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ የባህር ዳርቻ ለመሻገር ለሚፈልጉ ፍልሰተኞች ተመራጭ የመነሻ ቦታ አድርጓታል።
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-30
