ኮቪድ 19 ተጽዕኖ፣ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለው ጦርነት፣ የዋጋ ግሽበት የሕዝቡን ኑሮ በእጅጉ ከባድ ያደረጉ ክስተቶች እንደኾኑ ይገለጻል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳውና የበርካታ ዜጎች ራስ ምታት የሆነው ጉዳይ ደግሞ የቤት ኪራይ ዋጋ መናር ዋንኛው ነው። ይህ ጉዳይ አሁንም የኑሮአቸው ትልቁ ፈተና እንደኾነ ኑሮአችውን በኪራይ ቤት ያደረጉ ዜጎች ነግረውናል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዜጎች ላይ የሚደርሰውን የኑሮ ጫናን ለመቀነስ በመኖርያ ቤት ተከራዮች ላይ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ እና ተከራይን ማስለቀቅን የሚከለክል ደንብ አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
ይህ ደንብ በተለያዩ ጊዜአት እየተራዘመ አንድ ዓመትን አስቆጥሯል። ይህ ደንብ እየታየ ያለውን የቤት ኪራይ ጭማሪ እያረጋጋ እንዳልኾነ እና በሚገባ ተፈጻሚ መኾን እንዳልቻለም ነዋሪዎቹ ነግረውናል።
አቶ ተሀድሶ አበባው የቤት ኪራይ ጭማሪን የሚከለክለውን ደንብ ባወጣው በከንቲባ ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ዳይሬክተር ናቸው በጉዳዩ ላይ በሰጡን ምላሽ ደንቡ የበርካታ ቤት ተከራይ ዜጎችን ሕይወት ጫና አቅሏል ብለውናል በደንቡ ተፈጻሚነት ላይ ለተነሳው ቅሬታም ወረዳዎች ይህን ጉዳይ ከነዋሪዎች ጋር በቅርብተ በመኾን ያስፈጽማሉ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ።
ከደንቡ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ የቤት አከራዮችን ያማከለ እንዳልኾነ ነው። በዚህ ዐሳብ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን አቶ ተሀድሶ ጠይቀናቸው ቅሬታ ያለው አከራይ ከወረዳ እስከ ከንቲባ ጽ/ቤት ድረስ ቀርቦ ማቅረብ ይችላል ብለዋናል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚቀጥሉት 90 ቀናት ማንኛውም አከራይ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪን እንዳያደርግ ከልክሏል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-09-21
