ሀገሬ ቲቪ

“የጦርነት ቅዱስ የሰላም መጥፎ የለውም” የሲቪክ ማህበራት ጥምረት ፕ/ት

የዓለም አቀፉ የሰላም ቀን በሀገራችን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮች በተገኙበት ተከብሮ ውሏል።

በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የተ.መ.ድ. ተወካይ እና የሰባዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ካትሪን ሱዚ የዲጂታል ተግባቦቱ ጥላቻን ለማስፋት እና ለጽንፈኝነት መጠቀም እንደማይገባ ብሎም ለሰላም አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባው ጠቁመዋል። የሰላም ባህልን መፍጠር ልዩነት ባላቸው መካከል የሚደረግ ንግግርን መደገፍ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

ሀገሬ ቴ.ቪ. ያነጋገራቸው የሲቪክ ማህበራት ጥምረት ፕሬዝዳንት አቶ አቶ ታደለ ደርሰህ ደግሞ “የጦርነት ቅዱስ የሰላም መጥፎ የለውም” ያሉን ሲሆን መንግስት ከህወሃት ጋር እየተደረገ ያለውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት እና በአጭሩ ለመቋጨት የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የሲቪክ ማህበራትም በገለልተኝነት እና ህብረተሰቡን በማስተማር ሰላምን ለማምጣት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በሚል የተቋቋመው የትምራን ሲቪክ ማህበር የፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ወይዘሮ ማህደር ዳዲ ደግሞ ሰላምን ለማምጣት የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል ብለውናል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ ደግሞ ዘላቂ የሰላም ዕሳቤን ለማምጣት የሰላም ትምህርትን በትምህርት ስርዓቱ ማካተት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-09-21