ሀገሬ ቲቪ

የአዲስ ዓመት ዕቅዶቻችን ለምን አይቀጥሉም?

አዲስ ዓመት ሲመጣ ያቀድናቸውን ዕቅዶች የመፈጸም ተነሳሽነታችን በጊዜ ሂደት ይቀዛቀዛል ፤ ዕቅዳችንን የመፈጸማችንን ብርታት ተነሳሽነቱ ከውጭ ነው ከውስጥ የመጣው የሚለው ወሳኝ ነው። የጀመረነውን ከፍጻሜ ለማድረስ የውስጥ ተነሳሽነትን በማጠንከር መበርታት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

አዲስ ዓመት ሲለወጥ በሚፈጥርብን አዲስ የለውጥ ተነሳሽነት የተነሳ የማቀድ ዝንባሌ እንደሚኖረን የስነልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ቀን ቀንን ሲተካ ግን በዕቅዳችን የመቀጠላችን ተነሳሽነት እየተዳከመ ይመጣል። እኛም ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው አዲስ ዓመት ሲመጣ ቢያቅዱም ዕቅዳቸውን ለማስቀጠል እንደሚቸገሩ ነግረውናል።

ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው መምህር እና የስነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ያሬድ በአዲስ ዓመት ባገኘነው ተነሳሽነት የጀምርነው ዕቅድ ስለምን የአፈጻጸም ቀጣይነቱን ያጣል ላልናቸው ደግሞ ተነሳሽነቱ የመጣበት ምንጩ ይወስነዋል ያሉን ሲሆን ከውስጥ አምነንበት የጀመርነው ከሆነ የመፈጸም ዕድሉ የሰፋ ይሆናል ሲሉ ነግረውናል።

አዲስ ዓመት በውስጣችን በሚፈጥረው ተነሳሽነት የወጠናቸውን ዕቅዶች ለማስቀጠልስ ላልናቸው ደግሞ መበርታት ያስፈልጋል ሲሉ ለዕቅድ ተፈጻሚነት ጽናት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-09-22