የረዥም ጊዜ የድንበር ላይ ግጭት ኢራን እና ኢራቅን ወደ ጦርነት መርቷቸዋል። የኢራቁ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሳዳም ሁሴን የኢራኗን የነዳጅ ግዛት ኩዜስታን ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
በነዳጅ የበለጸጉት ሃገራት ጦርነት የታንከር ጦርነት ተብሎም ይጠራል። ይሄው የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት በሆኑት ኢራቅ እና ኢራን መካከል ለ7 አመታት የተደረገው ጦርነት የተጀመረው በዛሬዋ ዕለት በ1973 ዓ.ም. ነበር።
በሁለቱ ተቀናቃኝ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ኢራን እና ኢራቅ መካከል ተጀመሮ ለ7 ዓመታት የቆየው የኢራን ኢራቅ ጦርነት በ1970ዎቹ ነበር የተከሰተው።
በ1960ዎቹ መጀመሪያ እንግሊዝ ቀጠናውን የመልቀቅ ፍላጎቷን ካሳወቀች ጀምሮ በኢራን እና ኢራቅ መካከል የግዛት ድንበር አለመስማማቶች የውጥረት ምንጭ ሆነው ቆይተዋል። በኢራቅ ሳዳም ሁሴን ስልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ደግሞ በኢራን የነበረው የግዛት ጥያቄ ውጥረት ላይ አይናቸውን አሳርፈዋል።
በ1970ዎቹ መጀምሪያ የተቀሰቀሰው የኢራን አብዮት ቀደም ብሎ የተደረገን የሃገራቱን የድንበር ስምምነት ላይ ጥያቄ አስነስቷል። የድንበር ግጭቶችም በሀገራቱ መካከል መከሰት ጀመሩ። የኢራቅ በኢራን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ምልክቶችም መታየት ጀምረው ነበር።
ኋላም የኢራቁ ሳዳም ሁሴን በ1973 ዓ.ም. የድንበር ላይ ግጭቱን ወደ ታቀደበት የተደራጀ ጥቃት ቀየሩት። ግስጋሴያቸው የጎረቤት ሃገሯ ኢራን የነዳጅ ስፍራዎችን ለመቆጣጠር እና የሃብት ምንጭ ለማድረግ ሆነ። ቀድሞ በእንግሊዝ ቁጥጥር ስር የነበሩት የነዳጅ ስፍራዎች ከእንግሊዝ ቀጠናውን መልቀቅ በኋላ በ1960ዎቹ አጋማሽ በሀገራቱ መካከል የነበሩት የነዳጅ ዘይት ስፍራዎች በኢራን ቁጥጥር ስር ገብተዋል።
ይህ ግን ለሳዳም ሁሴን አስተዳደር የሚዋጥ አልሆነም። ከዛሬ 37 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት በኢራን ላይ ይፋ ጦርነት አወጁ።
የኢራቅ ጦር የኢራንን ድንበር ጥሶ በነዳጅ ወደ በለጸገችው እና በኢራን ቁጥጥር ስር ወደ ነበረችው ኩዜስታን ገሰገሰ።
የጎረቤት ሃገር ኢራቅ ጦር ወደ ሃገሪቱ ሰርጎ መግባት ለኢራን ዱብዳ ነበር። የገሰገሰው የኢራቅ ጦር ሌላ ከተማን መያዝ ቢችልም የነዳጅ ማጣሪያ ማዕከል የሆነችው ወሳኟን አባዳንን መያዝ አልተቻለውም ነበር።
የኢራቅ ጦር በሁለት ወራት ውስጥ ከኢራን እስከ 120 ኪ.ሜ. ድረስ ሰርጎ መግባት ቻለ። የጦሩ ግስጋሴ ግን ድንገተኛ በሆነበት ጠንካራ መከላከል ተገታ።
የኢራን የመንግስት ጦር (IRGC) የተፈጥሮ ሃብት ያላቸውን የኢራን ግዛቶች እየተቆጠጠረ የገሰገሰውን የኢራቅ ጦር እንዲያፈገፍግ አስገደደው። በ1974 ዓ.ም. ደግሞ የኢራቅ ጦር ተቆጣጥሯት የነበረችው ኮራምሻርን ለኢራቅ ጦር ለቀቀ።
ግስጋሴው በኢራናውያን የተገታው የኢራቅ ጦር የያዛቸውን ግዛቶች መልቀቅ ያዘ። በፈቃደኝነትም የያዛቸውን የኢራን ግዛቶች ለቆ የብዙ ጦርነቶች መቋጫ ወደሆነው የሰላም ስምምነት ፍላጎቱን አሳየ።
ሳዳም ሁሴን ግን በኢራን ትኩረት ለተሰጠው የእስላማዊ አብዮት እንቅፋት ተደርገው በመታሰባቸው በሃገራቱ መካከል ያለው ጦርነት እንዲቀጥል ሆኗል። የነዳጅ ማከማቸዋቻቸው ላይ ጭምር የሚሳኤል ጥቃት እርስ በርስ ይፈጻጸሙ ጀመር።
በነዳጅ አቅራቢነታቸው የሚታወቁት ሃገራት የነዳጅ መርከቦቻቸው ላይ ሳይቀር ጥቃት ይደራረሱ ጀመር። በዚህ ድርጊታቸው የዓለም አቀፉ የነዳጅ አቅርቦት ላይም በጊዜው ቀላል የማይባል ተጽዕኖን አሳድረዋል። ከ100 በላይ የነዳጅ ዘይት ታንከሮችም ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ሃገራቱ በነዳጅ የበለጸጉ በመሆናቸው ሳቢያ የታንከር ጦርነት እየተባለ በሚጠራው በዚህ ጦርነት ኢራቅ የጎረቤት አረብ ሃገራት የኩዌት፣ ሳውዲ አረቢያ እና ሌሎችም ብሎም የአሜሪካ እና ሶቭየት ህብረት ድጋፍ ነበራት። ከኢራን ጎን ግን የቆሙት ሶሪያ እና ሊቢያ ብቻ ነበሩ።
የነዳጅ ዘይት ላይ ጥቃቱ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ እንዲገባም ምክንያት ሆኗል። ኋላም የጦርነት የበላይነቱን ኢራቅ ወሰደች። ከዚህ ሁሉ በኋላም በ1980 ዓ.ም. የተ.መ.ድ. የጸጥታው ምክር ቤት ሃገራቱን ለተኩስ አቁም የሚያስገድድ ውሳኔ አሳልፏል። ኋላም የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ በአስገዳጅነት እንዲፈጸም ተደርጓል።
የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አውዳሚው ጦርነት እንደሆነ በሚነገርለት በዚህ ጦርነት የሃገራቱ ወንዶች ሁሉም በሚባል ደረጃ ታጥቀውበታል። ግልጽ መረጃዎች ባይኖሩም ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ ጉዳቶች ተመዝግቦበታል። የሞቱን ቁጥር ብልጫ ኢራን ብትወስድም ከ500 ሺ በላይ ሞት በሁለቱም ሃገራት በኩል ተመዝግቦበታል።
በአብርሃም በለጠ
2022-09-22
