ሀገሬ ቲቪ

እስራኤል ከፍልስጤም ጋር ያላት ግጭት እንዲፈታ ጥሪ አቀረበች

እስራኤል እና ፍልስጤም ጊዜን እየጠበቀ በሚነሳ ግጭት ዓለም የሚያውቃቸው ሀገራት ናቸው።በዚህ ግጭታቸው በርካታ ንጹኃን ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይህ ግጭታቸው ዛሬም ድረስ ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኝ ቀጥሏል።

በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ የእስራኤሉ ጠቅላይሚኒስትር ያኢር ላፒድ ይህ ግጭታቸው መፍትሔ እንዲያገኝ ጥሪ ማቅረባቸውን ፍራንስ24 ዘግቧል።

በዚህም በዓመታት ውስጥ በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግጭት መፍትሔ እንዲያገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሪ ያቀረቡ መሪ ኾነዋል።

ጠቅላይሚኒስትር ያኢር ላፒድ በንግግራቸው የሰላም ስምምነቱ በሁለቱ ወገኖች ሕዝብ መካከል መኾን አለበት ብለዋል። ይህ መኾኑ ለትውልድ ጠቃሚ ነው በማለት ገልጸዋል።

“ከፍልስጤም ጋር የሚደረገው ስምምነት ለሁለቱ ሀገራት ሕዝብ መኾኑ ለእስራኤል ደህንነት ኢኮኖሚ እንዲሁም ለቀጣይ ልጆቻችንን አስፈላጊ ነው ሰላም የምርጫ ጉዳይ አይደለም በእጅጉ አስፈላጊ እንጂ”

ሮይተርስ የሳቸውን ንግግር ተከትሎ ዋሱል አቡ ዮሰፍ የተባሉ የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት ነባር አባልን ምን ትላላችሁ ሲል አናግሮ ነበር የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር እርባና የለሽ ነው የሚል መልስ ዋሱል አቡ ዮሰፍ ሰጥተዋል። ማንም ይሁን ማንም የሁለቱን ሀገራት ሰላም የሚፈልግ መሬት ላይ የሚወርድ እና የሚተገበር መፍትሔ ነው ማምጣት ያለበት ብለዋል።

ቀደም ሲል የደረሱ ስምምነቶችን በማክበር፣ የሰፈራ መስፋፋትን በማስቆም እና ምስራቅ እየሩሳሌም የወደፊት የፍልስጤም ግዛት ዋና ከተማ መሆኑን በመቀበል ተግባራዊ ማድረግ አለበት" የሚል ሀሳቦችን የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት ሰንዝሯል።

ያኢር ላፒድ ይህን የሰላም ጥሪ በአንድ ጎን ያቅርቡ እንጂ በሌላው ጎናቸው ኢራንን የተመለከተ ጠንከር ያለ እና ጸብ አጫሪ መሳይ ንግግር አድርገዋል።

እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት እስራኤል "የሚያስፈልገውን ሁሉ" እንደምታደርግ የኢራንን ድርጊት በማውገዝ ተናግረዋል። የረጅም ጊዜ ተቀናቃኛችን ናት ያሏት ኢራን የኒውክሌር ማሳሪያ ሊኖራት አይገባም ብለዋል።

“ኢራን የኑክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት ለመከላከል ብቸኛው መንገድ በጠረጼዛ ዙሪያ ውይይት ሳይኾን አስተማማኝ የሆነ ወታደራዊ ኃይል በተጠንቀቅ እንዲቆም ማድረግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ይህንን ለማድረግ አቅሙ አለን ምንም የሚያስፈራን ነገር የለም ሲሉ ጠቅላይሚኒስትር ያኢር ላፒድ በተመድ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ ብቸኛ የኒውክሌር ማሳሪያ እንዳላት የሚነገርላት ኢራን በእስራኤል ዘንድ እንደስጋት ትታያለች።

እስራኤል በ1960 ዓ.ም በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ፍልስጤማውያን የኛ ናቸው የሚሉትን ምስራቅ እየሩሳሌም፣ ምዕራብ ባንክና ጋዛን ወደራሷ ማጠቃለሏን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት እስከዛሬ በደም መፋሰስ ውስጥ ይገኛሉ።

በሙሉጌታ በላይ
2022-09-23