ሀገሬ ቲቪ

ቅጽበታዊ ጎርፍን ለመከላከል ይረዳል የተባሉት ራዳሮች

አምና ብለን በተሻገርነው የ2014 ዓ.ም. የክረምት ወራት ከፍ ያለ የዝናብ መጠን የነበረበት ስለመሆኑ ተመልክተናል። ታዲያ ይህ የዝናብ ሁኔታ ቅጽበታዊ ጎርፍ እንዲከሰት ምክንያትም ሲሆን ተመልክተናል።

በዚህም ሳቢያ አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች በዚህ ምክንያት ለጉዳት ተዳርገው ነበር። ታዲያ ቅጽበታዊ የሆኑ ጎርፎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዳ የአየር ንብረት መከታተያ ራዳር አስፈላጊ ነው።

ይህ የአየር መቆጣጠሪያ ራዳር እስከ 250 ኪሎሜትር ድረስ ዙሪያውን ያለውን የደመና ሁኔታ እና ሊያመነጭ የሚችለውን የዝናብ መጠን አስቀድሞ ለማወቅ የሚረዳ ነው።

መሳሪያው በሀገራችን ኢትዮጵያ አንድ ብቻ መሆኑ ደግሞ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል እንዳይቻል እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።

ከመሳሪያ የሚገኙ መረጃዎች አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል በእጅጉ የሚጠቅሙ ስለመሆናቸው ያነሱት ኃላፊው፤ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በፍጥነት እየተለዋወጠ ያለውን የአየርሁኔታ በሚገባው ፍጥነት ለመከታተል ይረዳ ዘንድ ተጨማሪ የመቆጣጠሪያ ራዳሮች በመገንባት ላይ መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።

እየተገነቡ ካሉት ሦስት ራዳሮች መካከል አንደኛው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደስራ መግባቱን አቶ ክንፈ ነግረውናል። አንደኛው በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ ስራ የሚገባ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባም ሰምተናል።

እነዚህ ራዳሮች ከፍተኛ የዝናብ መጠን ያላቸውን አካባቢዎች በመሸፈን ቅጽበታዊ ጎርፍን አስቀድሞ ከመተንበይ ባለፈም ለበርካታ አገልግሎቶች ጥቅም የሚሰጡ እመሆናቸውን የተናገሩት አቶ ክንፈ ተቋማት ከእነዚህ የሚገኙ መረጃዎችን በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-09-23