ሳንታንዴር ባንክ 130 ሚሊዮን ዩሮ ለደንበኞች በስህተት መበተኑ ተሰማ፡፡ ባንኩ በስህተት ለ75 ሺሕ ደብተር ላላቸው የባንክ ተጠቃሚዎች ባለፈው ቅዳሜ ገንዘቡን መበተኑ ነው የተነገረው፡፡ የባንኩ ሠራተኞች የተበተነውን ገንዘብ ለማስመለስ እላይ እታች እያሉ ይገኛሉ፡፡ ጉዳዩን ከባድ ያደረገው ባንኩ ብሩን ያደለው በሌሎች ባንኮች ደብተር ውስጥ መሆኑን ታይምስ ጽፏል፡፡ ስህተቱ የተከሰተው ለ2 ሺሕ የንግድ አካውንቶች ሁለት ጊዜ ክፍያ በመፈፀሙ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን ያለው ባንኩ፤ሳናስበው የደንበኞቻችንን ገንዘብ ለሌሎች ባለደብተሮች አድለናል ብሏል፡፡ ባንኩ እንግሊዝ ውስጥ ካሉ ሌሎች ባንኮች ጋር በመተባበር የዘራውን ገንዘብ ለመሰብሰብ እንደሚሠራም ገልጿል፡፡ እንደ ታይምስ ከሆነ አንዳንድ ደንበኞች ከቀጣሪዎቻቸው ሁሉት ጊዜ ክፍያ ደርሷቸዋል። ነገር ግን አንደኛው ክፍያ የመጣው በመደበኛነት ከሚጠቀሙበት ባንክ ሳይሆን ከሳንታንዴር ባንክ መሆኑ ግርምትን አጭሯል፡፡ ታይምስ እንደጻፈው ባርክሌይስ፣ ኤችኤስቢሲ፣ ናትዌስት፣ ኮ-ኦፕሬቲቭና ቨርጂን መኒ በተሰኙት ባንኮች ነው የተጠቀሰው ገንዘብ ገቢ የተደረገው፡፡ ሳንታንዴር እኚህ ከላይ የተጠቀሱት ባንኮች በስህተት የገባውን ገንዘብ ከደንበኞቻቸው ሰብስበው ይመልሱልኝ ይሆናል የሚል ተስፋ ሰንቋል። ገንዘቡ የገባላቸው ሰዎች ጥቅም ላይ አውለውት ከሆነ እንዴት ነው ሊመልሱ የሚችሉት የሚለው አከራካሪ ሆኗል። ሳንታንዴር የገና ሲሳይ የወረደላቸውን ሰዎች ቀጥታ ደውሎ እባካችሁ ገንዘቤን መልሱልኝ ሊል እንደሚችል ተሰምቷል፡፡
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-31
