ሀገሬ ቲቪ

የመስቀሉ ፍለጋ

መስከረም ለኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ወርህ ናት። በመስከረም መስኩ በአረንጓዴ ይሸፈናል። አደይ ይሏት አበባ ለዓመት ድራሿ እንዳልጠፋ በየቦታው በብዛት ትታያለች።

የመስቀል ወፍስ ብትሆን ከጠፋችበት ብቅ ብላ መስቀል ደርሷል ስትል ልታበስር ይመስል ትከሰታለች። ባለቅኔው መንግስቱ ለማ የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ፣ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ ማን ያውቃል፤ እንዳሉት መሆኑ ነው። ወሩ መስከረም ነው።

በልዩ ድባብ የደመራ ቀንን ለማፍካት ደግሞ ችቦ በየስፍራው ይዘጋጃል። በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በዓሉ በድምቀት ይከበራል። ይሄው የመስቀል በዓል አከባበር በዩኔስኮ የተመዘገበ የማይዳሰስ ቅርሳችን መሆኑም ሳይዘነጋ።

ይህ ሁሉ ሽር ጉድ መነሾው ምንድነው ካልን በአማኞች ዘንድ እንዲህ የሚል ምላሽ አለ። ምላሹን ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ንግስት ዕሌኒ የተቀበረውን የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀልን የፈለገችበት ታሪክ መታሰቢያ ነው ብለውናል።

ዋዜማው ደመራ ዋናው ዕለት መስቀል ተብሎ እንደሚጠራ ያስታወሱት ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ስለበዓሉ ትውፊታዊ ታሪክ የነጋዴ ሚስት የነበረችው እና መስቀሉን በመፈለጉ ትልቅ ሚና የነበራት ንግስት ዕሌኒ በሃሰተኛ ጥርጣሬ ምክንያት በባለቤቷ ባህር ላይ ተጥላ የቢዛንታይን ንጉስ አግኝቷት የንጉሱ ሚስት ለመሆን መብቃቷን ብሎም ንጉስ ቆስጠንጢኖስን መውለዷን ይናገራሉ።

ንግስት ዕሌኒ በልጇ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ ላይ ክርስትናን በማስተማር በኩል ተጽዕኖ ስላማድረጓም ይገልጻሉ። በመጨረሻም ንጉስ ቆስጠንጢኖስ ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ ልጄ ክርስትናን ከተቀበለ የሚለውን የእናቱ ስለት የሆነውን እና ክርስቲያን ባልሆኑት የተቀበረውን የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል በመፈለጉ በኩል እናቱን በትልቁ ማገዙን ነግረውናል።

የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል የተቀበረበትን ስፍራ ለማወቅ ደመራ እንዲደመር ተደርጎ እንደነበር ለማሰብም ዛሬም በአማኞች ዘንድ ደመራ ይደመራል።

ደመራው የተደመረበት ዕለት መስከረም 16 መስቀሉን ፍለጋ ቁፋሮ የተጀመረበት ዕለት መስከረም 17 መሆኑን የቤተክርስቲያንን ታሪክ ጠቅሰው የነገሩን ዲያቆን ቴዎድሮስ፣ ቁፋሮው ተጠናቆ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቢሆንም ለመገኘቱ ቁፋሮው የተጀመረበትን መስከረም 17ን በድምቀት አክብረን መጋቢት 10ን አስበን እናሳልፈዋለን ብለውናል።

እኛም መልካም የመስቀል በዓል አልን።

በአብርሃም በለጠ
2022-09-26