ሀገሬ ቲቪ

ልጆች እይታቸውን ከማጣታቸው በፊት ዓለም እያዩ ነው

ቤተሰብ። ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጡት ነገር ነው።

ወላጆች ለልጆቻችው የተሻለ ዓለምን ለመፍጠር ቀን ከሌት ያለእረፍት ይደክማሉ ይለፋሉ። በተለይ ደግሞ ዓለሞቼ የሚሏቸው ልጆቾ በጊዜሂደት እያደገ የሚሄድ ህመም አለባቸው መባል ለወላጅ ቀላል አይደለም።

አሁን የምንነግራችሁ ታሪክም ይህንን ከባድ ፈተና በብልሃት እያለፉ ስላሉ ወላጆች ነው። በካናዳ ኑሯቸውን ያደረጉት ኤዲት እና ሰባስትያን በትዳር ዘመናቸው አራት ልጆች አፍርተዋል። ደስተኛ የሆነን ቤተሰብንም ይመራሉ።

ታዲያ ከአራቱ ልጆቻቸው ውስጥ ሦስቱ በግዜ ሂደት እይታን የሚያጠፋ በዘር የሚተላለፍ የአይን ህመም እንዳለባቸው አወቁ። ህመሙ ሬቴናይቲስ ፒግመንቶሳ ይሰኛል።

የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት በሽታው በሬቲና በሚሰኘው የአይናችን የውስጠኛ ክፍል ላይ ያሉ ሴሎች በጊዜ ሂደት ቀስ ብለው እንዲበጣጠሱ በማድረግ እይታን ያሳጣል።

ይህ የበሽታ አይነት አብዛኛውን ግዜ ምልክት የማያሳይ ስለመሆኑም ይናገራሉ። ታዲያ እነኤዲት እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም ጓዛቸውን ሸክፈው ተነሱ እንጂ።

ልጆቻቸው እይታቸውን ከማጣታቸው አስቀድመው ዓለምን በአይናቸው አይተው በአዕምሯቸው ውስጥ ስለው እንዲያስቀምጧት ለማድረግ በማሰብ።

ማያ፣ ኮሊን እና ሎሬንት አሁን ዓለምን በአዕምሯቸው ለማስቀረት በጉዞ ላይ ናቸው።

ባለሙያዎች ሰዎች ዓለምን ከመፅሐፍ ላይ በማንበብ በአዕምሯቸው ውስጥ እንዲስሏት ይመክራሉ።

“ዓለምን ከመፅሐፍ ላይ አንብበው እንዲያቋት በጭራሽ አላደርግም ስል ለራሴ ቃል ገባሁ። ዝሆኖችን እና ቀጭኔኦችን በአይኗ እንድታያቸው ይዣት እሄዳለው።”

አባት እና እናት ከዓመት በላይ የሚቆይ ዓለምን ዞሮ የመጎብኘት ፕሮግራም እያደረጉ ይገኛሉ።

“ስለ ጉዳዩ ስናስብ በቻልነው መጠን ሁሉ እያንዳንዱን የዓለም ዳርቻ ልናሳያቸው ፈለግን፤ የምታምረዋን ዓለም እንዲያዩ እና በአዕምሯቸው የተዋቡትን ነገሮች ስለው እንዲያስቀምጧትለማድረግ።”

ልጆቼ በሚሆንባቸው ነገር እንዲደነግጡ አልፈልግም የምትለው እናት፤ በቻሉት መጠን ዓለምን ዞረው ከማየት ባለፈም እያንዳንዱን መዳረሻ የህይወትን መንገድ ለልጆቻቸው ለማስተማር እየተጠቀሙበት ስለመሆኑም ትናገራለች።

አሁን በሦስት አህጉሮች ስድስት ሀገራትን አዳርሰዋል። ገና የተሻለች እና የምታምረዋን የዓለም ክፍል ለማዳረስ ጉዟቸው አላለቀም።

ነገም በመንገድ ላይ ናችው። ይህ ለቤተሰብ ሲባል የሚከፈል ነው እና።

በሳምሶን ገድሉ
2022-09-26