ከዝሆኖች እስከ ንስር፣ ከእንስሳት ጀርባ እስከ ሰማይ በራሪ አውሮፕላኖች የዚህች ሀገር መገለጫዎች ናቸው። በያኔ በደጉ ዘመን በአፍሪካ ጉልበታም አየር መንገድም ነበር።
አሁን ይህ ሁሉ ታሪክ ብቻ ነው። የራሳቸው የሆነ አየር መንገድ ከሌላቸው ሀገራት ተርታ ውስጥ ከተመደበች ሁለት አስርት ዓመታት እንደቀልድ አልፈዋታል።
አሁን ግን መልካም ዜና የተሰማ ይመስላል፤ የሀገር ቤቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻን የያዘበት አዲስ አየር መንገድ ልታቋቁም ነው።
በ1951 ዓ.ም. የራስዋ አየር መንገድ ባለቤት የነበረችዋ ናይጄሪያ በተለያዩ ምክንያቶች አየር መንገዷን በ1996 ዓ.ም ዘግታለች። ታዲያ ናይጄሪያ እጇን አጣጥፋም አልተቀመጠችም አየር መንገዷ ዳግም ህይወት እንዲዘራ ለማድረግ የአፍሪካ እና ሌሎች አየር መንገዶች በአቭየሽኑ ዘርፍ በናይጄሪያ እንዲሰማሩም ስትማፃን ቆይታለች።
ለዚሁ ሲባል የወጣውንም ጨረታ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማሸነፉን ሮይተርስ አስነብቧል። የሀገሪቱ የአቭየሽን ሚንስትር ሃዲ ሲሪካ የአየር መንገዱን ድርሻዎች በተመለከተም ተከታዩን ብለዋል።
“የግልፀኝነቱ ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ ሁሉም ነገር በፖርታሉ ላይ የሚጫን ስለሆነ ሁሉም ሊመለከተው ይችላል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቴክኒካዊ እና ፋይናንሻል ጉዳዮች ላይ 86.7 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል።”
“የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻን ይወስዳል፣ የናይጄሪያ የግል ባለሀብቶች እና የናይጄሪያ ሶቨርን ፈንድ 46 በመቶ የሚይዙ ይሆናሉ ቀሪው 5 በመቶ ደግሞ በናይጄሪያ መንግስት ስር ይሆናል።”
በዚህ ስምምነት መሰረትም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ያሉት ባለድርሻዎች፣ እንደ ድርሻቸው መጠን 300 ሚሊዮን ዶላር፣ ለአየር መንገዱ ወጪ ያደርጋሉ ተብሏል።
ባለንበት የፈረንጆች ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች መላው በጠፋባቸው በዚህ ሰዓት 937 ሚሊዮን ዶላር ማትረፉ ችሏል።
አጠቃላይ ገቢውንም ወደ 79 በመቶ ከፍ ማድረግ ችሏል። ይህም አጠቃላይ ገቢው 5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ያሳያል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለቤት የሆነበት በናይጄሪያ የሚመሰረተው አዲሱ አየር መንገድ በምዕራብ አፍሪካ የአቭየሽን ማዕከል እንዲሆንም ታስቧል።
በቀጣይ አራት ዓመታት ውስጥ 30 አውሮፕላኖች ይኖሩታልም ተብሎ ይጠበቅል። አየር መንገዱ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መገባደጃ ላይ ወደ ስራ ለማስገባት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉም ይገኛሉ። በቅድሚያ 6 ቦይንግ 737 አውሮፕላኖችን ለመግዛት እቅድ መያዙም ተሰምቷል።
የሞሀመዱ ቡሃሪ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ሊተገብራቸው ቃል ከገባቸው ተግባራት መካከል አየር መንገዱን ዳግም ወደ ስራ ማስገባት እና የአቭየሽኑን ዘርፍ ለግል ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ ይገኝበታል።
ታዲያ አዲሱ አየር መንገድ ኪሳራ እንዳይገጥመው የተሰሩትን ስራዎች ሚንስትሩ ሲሪካ እንዲህ ገልፀዋቸዋል።
“በቡሃሪ መንግስት በኩል ከ2015 እስከ ዛሬ ድረስ የፓሴንጀሮቻችንን ቁጥር በአንድ አራተኛ ከፍ አድርገናል፣ አየር ማረፊያዎቻችንን እና የአየር መንገዶችን ቁጥር በእጥፍ ጨምረናል፣ የአብራሪዎቻችንን እና ኢንጂነሮቻችንን ቁጥርም እንደአው እጥፍ አርገናል እንደማስበው መልካም ስራዎችን ሰርተናል።”
የአየር መንገዱ የማስጀመሪያ ወጪ 8.8 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተነግሯል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-09-28
