ሀገሬ ቲቪ

በጃፓን በራሪ ሞተር ሳይክል ተሰራ

ድሮ ድሮ አባቶቻችን ከሌለ በ እግር ካለ ደግሞ እንደፈረስ ያሉ እንሳሳዎችን ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ይጠቀሟቸዋል ። ቀስ በቀስ ምድር እየሰለጠነች ቴክኖሎጂ ጀባ በሚለን አዳዲስ ነገሮች የአኗኗር ሁኔታዎችችን እየቀለሉ መጡ ።

በእግር እና በእንስሳት ከመጓዝ ወደ ተሽከርካሪ መኪናዎች አለፍ ሲልም በአየር ተንሳፋፊ ወደሆኑት አውሮፕላኖች ተሸጋገርን። ስለመጓጓዣዎች ይህን ያህል ያልናችሁ ያለ ምክንያት አይደለም ከወደ ጃፓን አንድ አዲስ ነገር ብንሰማ ነው ።

ጃፓን ለምን ፕሌን ብቻ በአየር ይበራል በማለት መሰል በአየር ላይ ተምዘግዛጊ ሞተር ሳይክል በመስራት ለገበያ አቅርባለች።

ይህ በአየር ላይ ተንሳፋፊ የሆነ ሞተር ሳይክል በጃፓን ስታርትአፕ ኤርዋይንስ ቴክኖሎጂ የተሰራ ሲሆን ኤስቱሪዝሞ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል ።

ሞተር ሳይክሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ለ ዕይታ የቀረበው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተደረገ ዴትሮይት አውቶ ሾው ላይ ሲሆን በዓለም ላይ የመጀመሪያው ተንሳፋፊ ሞተር ሳይክል የሚል እውቅና ተሰጥቶታል ። በሰዐት 100 ኪ.ሜ መብረር እንደሚችልም ተገልጿል።

ይህ ስሪት በተሽከርካሪዎች መብዛት እና በመንገዶች ጥበት የተነሳ የሚፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍ ታስቦ የተሰራ ሲሆን ብዙዎች የትራፊክ መጨናነቅ የሚያድርስባቸውን ጫና ሊቀንስ የሚችል ስራ በመሰራቱ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል ።

ታዲያ ይህ በራሪ ሞተር ሳይክል አሁን ላይ በ 777ሺ የ አሜሪካ ዶላር ወይም በኢትዮጵያ ዕለታዊ ምንዛሬ 40 ሚሊዮን ብር ለጃፓን ገበያ የቀረበ ሲሆን በቅርብ ጊዜት መሸጫውን ወደ 50 ሺ የ አሜሪካ ዶላር በመቀነስ እንዲሁም የምርቱን መጠን በማሳደግ በመላው አለም ለማሰራጨት ማቀዳቸውን የኤርዊንስ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ሹሄ ኮማትሱ ተናግረዋል ።

በዮሴፍ ከበደ
2022-09-28