ሀገሬ ቲቪ

ከ 5 ሺህ በላይ ሕገ-ወጥ ማስታወቂያዎች ተወገዱ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የውጭ ማስታወቂያ ደንብ ማጽደቁ ይታወሳል። ደንቡ በቢል ቦርድ፣ በማስታወቂያ ሰሌዳ፣ በኤሌክትሮኒክ ስክሪን ወይም በተንቀሳቃሽ ምስል የሚሰራጭ፣ እንዲሁም በሕንጻ፣ በግድግዳ፣ በተሽከርካሪ፣ የሚሳል፣ የሚፃፍ፣ የሚለጠፍ ወይም የሚተከልን ማስታወቂያን ከባለስልጣኑ ፈቃድ ሳያገኙ እና በተገኘው ቦታ መለጠፍን የሚከለክል ነው።

እኛም የዚህ ደንብ አፈጻጽም ምን ይመስላል እንደታሰብ እየተከናወነ ነው ወይ ስንል ጠይቀናል። ደንቡ ከወጣ በኋላ በዋና ቦታዎች ላይ የነበሩ ከ 5 ሺህ በላይ ሕገወጥ ማስታወቂያዎች እንዲጸዱ መደረጉን የተቋሙ የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥና ክትትል ዳይሬክተር የኾኑት አቶ አዲሱ መለሰ ነግረውናል።

ይህ ደንብ የመውጣቱ ምክንያት በተዘበራረቀ ሁኔታና ፈቃድ ሳይኖር የሚሰቀለው የውጪ ማስታወቂያ የከተማዋን ውበት እና ገጽታ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለማስወገድ እንደኾነ ተገልጿል።

በዚህ ረገድ የውጪ ማስታወቂያዎች ለመትከል የሚያገለግሉ ወሳኝ ቦታዎችን ከዚህ በሁላ ተቋሙ በሚያወጣው ጨረታ ነው ማግኘት የሚቻለው በተጨማሪ በየፖሉ እንደፈለጉ ወረቀቶችን መለጠፍ ተከልክሏል።

መመሪያውን ተፈጻሚ በማያደርጉ አካላት ላይ የገንዘብ መቀጮ ጀምሮ ሊሎች አስተዳደራዊ ቅታት ይጠብቃቸዋል። ደንቡ ከወጣ በኋላ ከ 2 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የውጭ ማስታወቂያድርጅቶች ፈቃድ ተሰጥቷል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-09-29