ሀገሬ ቲቪ

በመጸዳጃ ቤት ራሷን የወሸበችው አሜሪካዊት

በረራ ላይ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባት ተጓዥ ለሰዓታት በመጸዳጃ ቤት ራሷን መወሸቧ ተሰምቷል፡፡ አሜሪካዊቷ መምህርት በረራ ላይ ሳለች ባደረገችው ምርመራ ቫይረሱ እንዳለባት ስታውቅ ነበር በፈቃዷ ለአምስት ሰዓታት መጸደጃ ቤት ውስጥ የቆየችው። ማሪሳ ፎቲዮ የተባለችው መምህርት ከአሜሪካ ቺካጎ ወደ አይስላንድ እየተጓዘች ሳለ ጉሮሮዋን ስለከረከራት ቦርሳዋ ውስጥ ይዛው በነበረ የኮቪድ-19 መመርመሪያ ራሷን ስትፈትሽ ቫይረሱ እንዳለባት አውቃለች። በረራው እስከሚጠናቀቅ ድረስም በመጸዳጃ ቤት በበረራ አስተናጋጆች ምግብ እና ውሃ ቀርቦላታል፡፡ ከበረራው በፊት የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤቷን ለአየር መንገዱ ማቅረብ አለማቅረቧን ኤንቢሲ ኒውስ ያለው ነገር የለም፡፡ መምህርቷ በአውሮፕላኑ መጸዳጃ ቤት ሳለች ቪድዮ ቀርጻ ቲክቶክ በተሰኘ የማህበራዊ ሚዲያ መልቀቋም ተነግሯል፡፡ ተንቀሳቃሽ ምስሉንም ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል፡፡ አይስላንድ ስትደርስ ሆቴል ውስጥ ለይቶ ማቆያ መግባቷም ነው የተነገረው ፡፡ አሜሪካን ጨምሮ በሌሎችም አገሮች አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን በፍጥነት እየተሰራጨ ይገኛል። በአሜሪካ በአንድ ቀን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በአማካይ 277 ሺሕ ደርሰዋል፤ይህም ወረርሽኙ ከተነሳ ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው። በወረርሽኙ ሳቢያ ሆስፒታል የሚገቡና ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር ግን አሁንም አነስተኛ ነው። በኦሚክሮን ምክንያት በርካታ በረራዎች እየተሰረዙ ሲሆን፤ አሜሪካ ውስጥም 1ሺሕ 100 በረራዎች ተሰርዘዋል።

በሀገሬ ቲቪ
2021-12-31