ሀገሬ ቲቪ

ረሀብን ለመዋጋት ሰላም ያስፈልጋል ተባለ

795 ሚሊዮን ሰዎች በመላው ዓለም፣ በአፍሪካ 286 ሚሊዮንን የሚሻገሩ ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ የላቸውም። በአፍሪካ ያላው ቁጥርም የአህጉሪቱን 20 በመቶ የሚሆን ህዝብ ቁጥርን ይሻገራል።

በአየር ንብረት ለውጥን ሳቢያ ተደጋጋሚ የዝናብ ማጣት የያስከተለው ድርቅ የደቆሳት አህጉር አፍሪካ፤ በውስጧ ያለው የህዝቦቻ አለመረጋጋት እና የእርስ በእርስ ጦርነት ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል።

ታዲያ በአህጉሪቱ ያለው የምግብ ቀውስ ያሳሰበው የአለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ከሰሞኑ በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ መክሯል። በ2016 ዓ.ም. ረሀብን ዜሮ ለማድረግ ያለመው ድርጅቱ ለምግብ እጦት ዘላቂ መፍትሄው ሰላም እንደሆነ እስታውቋል።

የአለም የምግብ እና ግብርና ድርጅት ተወካይ የሆኑት አቶ አበበ ኃይለ ገብርኤል ከአህጉሪቱ ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው በዚሁ ምክክር ላይ ነው ይህንን የተናገሩት።

ዘላቂ የሆነን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ከፈለግን ሰላም አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

“በሶማሊያ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው። በተከታታይ ከአራት አመታት በላይ ድርቅ ተከስቶ የነበረ ሲሆን ይህም በህዝቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።”

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከቀያቸው ያሰደደው በአፍሪካ ቀንድ ያለው ረሀብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ከሞት አፋፍ ላይ አድርሷቸዋል።

በከብት እርባታ እና በእርሻ ስራ ኑሮውን የሚገዋፍ የቀጠናው ማህበረሰብ ላለፉት ሦስት ዓመታት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ሰማይ ሲሳይዋን ነፍጋተው ሰብላቸውን አጥተዋል፤ ከብቶቻቸውንም በህይወት ለማቆየት የሚሆን ውሃ እና መኖን በማጣታቸው እይኖቻቸው ስር አሸልበዋል።

በአቡጃ የተደረገው ምክክር በመላው አፍሪካ የሚገኙ ለርሀብ የተጋለጡ ዜጎችን ለማዳን ከዘመቻ እና ከእርዳታ የዘለለ ተግባርን የሚጠይቅ እንደሆነ ተነስቷል።

“FAO ከአንዳንድ ከለጋሽ ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር ለተጎዳው ክልል አርሶ አደሮች የሚቀርብ ማዳበሪያ ገዝቷል ነገር ግን ይህ ዘላቂ መፍትሄ አይደለም። ዘላቂው መፍትሄው መደበኛ ህይወት እንዲቀጥል ሰላምን ማረጋገጥ ነው።”

ላለፉት አስርት ዓመታት በሶማሊያ ማባሪያ ያጣው ጦርነት እና አልስተካከል ያለው የአየር ሁኔታ ሀገሪቱን በ10 ዓመታት ውስጥ ታይቶ ላልታወቀ ድርቅ አሳልፈው ሰጥተዋታል።

በቅርቡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ የሀገሪቱ አጋር ድርጅቶች ሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ስጋት ላይ የጣለውን ረሃብ ለመከላከል የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው አይዘነጋም።

በሳምሶን ገድሉ
2022-09-29