አበርክቷቸው ታላቅ ነው ለተባለላቸው ሰዎች የሚሰጠው የኖቤል ሽልማት መድረክ ላይ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ለመንገስ ሽልማቱ አንድ ብሎ ከጀመረበት ጊዜ 49 ዓመታትን መጠበቅ ነበረባቸው። ያም ቢሆን ለሰላም አበርክቷቸው የተሰጠ ነበር።
በምርምሩ ዘርፍ እስከ 1972 ዓ.ም. አልበርት ካሙስ በስነ ጽሁፍ ዘርፍ የኖቤል ሽልማትን ከማግኘቱ በስተቀር ማንም ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው ሰው የኖቤል ሽልማቱን አልወሰደም።
ዊልያም አርተር ሌዊስ ግን በምጣኔ ሃብት ዕድገት ጥናቱ እና ያደጉ እና በጥቂቱ ያደጉ ሃገራትን የንግድ ትስስርን ከግብርና ምርታማነት ደረጃቸው ጋር ያስተሳሰረ የምጣኔ ሀብት የፈጠራ ንድፉ ሳቢያ የኖቤል ሽልማትን በመውሰድ የመጀመሪያው ሆኗል።
ይሄው በምርምሩ ዘርፍ የመጀመሪያው የኖቤል ተሸላሚ ጥቁር ቆዳ ቀለም ያለው ተመራማሪ ዊሊያም አርተር ሌዊስ በልማት ምጣኔ ሀብት (Development Economics) ዘርፍ የታወቀ ምሁር የነበረ ሰው ነው። የኖቤል ሽልማትን ከማግኘቱ በተጨማሪ በዘርፉ ከ80 በላይ ቴክኒካዊ ስራዎች ባለቤት እና የ12 መጻህፍት ደራሲም ነው።
አርተር ሌዊስ የተወለደው በ20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ሴንት ሉሽያን ተብላ በምትጠራዋ ስፍራ በብሪቴን ምዕራብ ኢንደስ ነበር። የመምህራን ልጅ የነበረው አርተር ሌዊስ በ14 ዓመቱ የመንግስት የትምህርት ዕድልን አሸንፎ በእንግሊዝ ትምህርቱን ለመከታተል ተጉዟል። በ18 ዓመቱ የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስን ተቀላቅሏል።
ገና በአፍላ ዕድሜው ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀለው አርተር ሌዊስ በ1930ዎቹ መጀመሪያ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ የፒ.ኤች.ዲ ጥናቱን አጠናቆ በዚያው በለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት ለ9 ዓመታት መምህር ሆኗል።
በእንግሊዝ ለንደን ጥቁር መምህርን ማየት ብርቅ በነበረበት በዚያ ዘመን የመጀመሪያው ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ሰው ሆኗል። በማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፕሮእፌሰር በመሆንም በሀገሪቱ የዩኒቨርሲቲ ታሪክ ትልቁን ስፍራ መያዝ የቻለ የመጀመሪያው ጥቁር ሰው ሆኗል።
አርተር ሌዊስ በእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች ከማስተማሩ በተጨማሪ ለብዙ የአፍሪካ፣ ኤስያ እና ካሪቢያን ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የዕድገት ምጣኔ ሀብት አማካሪ በመሆን አገልግሏል። ለሶስት ዓመታትም የካሪቢያን ልማት ባንክ ኃላፊ ሆኖ አገልግሏል።
የምርምር አበርክቶዎቹን በማንቼስተር ዩኒቨርሲቲ ሳለ አብዝቶ የሰራው አርተር ሌዊስ በምጣኔ ሀብቱ (Economics) ዘርፍ ባላደጉት ሀገራት ላይ ትኩረቱን በማድረግ አዲስ አተያይን በዘርፉ ፈንጥቋል።
በምጣኔ ሀብት ምርምር ዘርፉ በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ስለጻፈው ስራው አበርክቶው በ1972 ዓ.ም. ደግሞ የኖቤል ሽልማትን መውሰድ ችሏል። በስራዎቹ አርተር ሌዊስ ትምህርት እና ማህበራዊ ዕድገት ለለውጥ አስፈላጊ መሆናቸውን አስምሮባቸዋል።
በሌላ በኩል ይህ ሰው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና ከዚያ በኋላም የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ቢሮ ከቅኝ ግዛቶቿ ጋር ለነጻነታቸው በሚያደርጉት ዝግጅት ስለምታደርገው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እና ከዚያም በኋላ ነጻ ለሆኑት ሀገራት የምጣኔ ሀብት አማካሪያቸው ነበር።
ለአብነትም ጋና ነጻነቷን ካገኘች በኋላ የመጀመሪያውን የምጣኔ ሀብት ዕቅዷን ስትነድፍ ዋነኛ አማካሪዋ አርተር ሌዊስ ነበር። በ1983 ዓ.ም. በ76 ዓመቱ እስኪያርፍም በዘርፉ አበርክቶውን አላቋረጠም ነበር።
በአብርሃም በለጠ
2022-09-29
