ሀገሬ ቲቪ

ደራሲ ኤሊ ዊሰል የተወለደበት ቀን

በዛሬዋ ዕለት መስከረም 20,1921 ዐ.ም በሮማኒያ ተወለደ ። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነው ። የኖቤል የሰላም ሽልማት ይገባሃል ተብሎ በ እጁ አስገብቷል ፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ከፍተኛ ስቃይን አሳልፏል ።

በዛን ጊዜ ከነበረው ጭፍጨፋ በተዐምር በመትረፍ ዐለማችን አሉኝ ከምትላቸው ደራሲያን ውስጥ አንዱ ሆኗል ፤ ስራዎቹ በአስገራሚ ሁኔታ ከፍተኛ ሽያጭ አላቸው። ደራሲ ኤሊ ዊሰል ።

በግንቦት ወር በ1944 ዐ.ም ናዚዎች የ15 ዓመቱን ዊሰል እና ቤተሰቦቹን ካረፉበት ቤት በማውጣት ፖላንድ ወደሚገኘ አንድ ማጎሪያ ካምፕ አስገቧቸው ።

ካምፑ ስቃይ የበዛበት ነበርና በገቡ በቀናት ውስጥ የዊሰል እናትና እህት አረፉ ። ከጊዜያት በኋላ እሱና አባቱ ከነበሩበት ካምፕ ጀርመን ወደሚገኝ ሌላ ማጎሪያ ተዘዋወሩ። ዊሰል ከአባቱ አባቱም ከዊሰል ውጪ ሌላ ደራሽ በሌለበት ስፍራ አባትየው አልቻለምና እስከወዲያኛው አሸለበ ። ያ ጨቅላ ብቻውን ቀረ ።

ናዚ በወቅቱ ባደረገው ጭፍጨፋ በርካታ ንጹሃንን ገደለ ። ነገር ግን የዛሬው ዕውቁ ደራሲ ከዛ ጭፍጨፋ በተዐምር ተረፈ ። ከጦርነቱ በኋላ ዊሰል በፈረንሳይ ወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ በመግባት ትምህርት የተማረ ሲሆን እድሜው ለስራ ሲደርስም በፈረንሳይ የዜና ማሰራጫ ማዕከል ውስጥ በጋዜጠኛነት መሥራት ጀመረ።

ዊሰል በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ያሳለፋቸውን አሰቃቂ ጊዜያት ለራሴም ቢሆን ደግሜ አላስባቸውም በማለት ለብዙ ጊዜያት ለማንም ሳይናገር አሳልፏል ። የጋዜጠኝነት ስራ በመጀመረበት ጊዜ ግን ይህን ታሪክ ለህዝብ ማድረስ አለብኝ በማለት ያኔ የገባውን ቃል አጠፈ ። በወቅቱ ያሳለፋቸውን የሱንና የቤተሰቡን ታሪኮች ጽፎ ለህትም አበቃ ።

ታዲያ ዊሰል በካምፖች ውስጥ ያሳለፋቸውን አሳዛኝ ታሪኮች በመጽሀፉ እንደወረደ ቢያሰፍራቸውም በወቅቱ የነበሩ አሳታሚዎች ስለ ዕልቂት ማንበብ የሚፈልግ ሰው የለም በማለት መጽሀፉን ለማሳተም አልፈለጉም ።

በመጨረሻም መጽሃፉ በ1960 ዓ.ም. "ላ ኑይት" በሚል ርዕስ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ታትሞ ወጣ ። ታዲያ መጽሀፉ ለገበያ በቀረበበት ጊዜ አሳታሚዎች ካሉት በተቃራኒ በ ወረፋ መሸጥ ጀመረ ።

ከ 2 ዐመት በኋላም Night ወይም ለሊት በሚል ርዕስ በ እንግሊዘኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለገበያ ዋለ ። በታተመ በጥቂት ጊዜያት ውስጥም በሚሊየን የሚቆጠሩ ዕትሞች ሰሸጡ ከ30 በላይ ሀገራትም በቋንቋዎቻቸው አስተርጉመው ለገበያ አዋሉ። ያኔ መጽሀፌን አሳትሙልኝ እያለ ሲጠይቅ የነበረው ሰው በ ዐለም ላይ ዝናው ናኘ ።

ዊሰል ከዚህ መጽሀፍ በኋላ የፍትሕ መጓደልን በመቃወም በተለያዩ የ ዐለማችን ክፍል በመዞር ንግግር አድርጓል ። በደርዘን የሚቆጠሩ ልብ ወለድና ልብ ወለድ ያልሆኑ ጽሑፎችንም አበርክቷል ።

ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን የጅምላ ጭፍጨፋ መታሰቢያ ሙዚየም እንዲመሰረት ከፍተኛውን አስተዋጾ አበርክቷል ። የ1986 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን አጊንቷል። በመጨረሻም በተወለደ በ 87 ዐመቱ ሐምሌ 2, 2008 ዐ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ።

በዮሴፍ ከበደ
2022-09-30