ዴንማርክ እንደምዕራባውያኑ የዘመን ቀመር በ2030 አውሮፕላኖቼ ነዳጅ መጠቀም ያቆማሉ አለች። የሀገሪቱ መንግስት ሁሉንም የሀገር ውስጥ በረራዎች ከነዳጅ ውጭ የማድርግ ውጥን ይዟል። ለአየር ንብረት ለውጥ በነዳጅ ኃይል የሚንቀሳቀሱት የመጓጓዣ ዘዴዎች ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሜቴ ፍሬድሪክሰን በአዲስ ዓመት ንግግራቸው ላይ "በረራዎችን አረንጓዴ ማድረግ" እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ይህንን ያለችዋ ሀገር በምን መንገድ በረራዎቿን ከነዳጅ ፍላጎት ነጻ እንደምታደርግ ብልሀቱን እንዳላገኘችም አምናለች። ከዚህ በተጨማሪም አዲስ በጀመረው የፈለንጆቹ ዓመት ላይ ከፍተኛ ብክለት ለሚያስከትሉ አውሮፕላኖችን የአየር ማረፊያ ክፍያ ለመጨመር ማቀዱን የሀገሪቱ መንግሥት አስታውቋል። ዴንማርክ በ2030 የምትለቀውን የካርበን መጠን 70 በመቶውን የማስቀረት እቅድን አላት። ወይዘሮዋ እንዳሉት ታዳሽ የኃይል ምንጭ የሚጠቀሙ በረራዎችን መፍጠር አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን የሀገሪቱ ተመራማሪዎች እና የፈጠራ ኩባንያዎች ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ግዙፉ የአውሮፓው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ኤርባስ በ2035 በሃይድሮጂን የሚነዱ አውሮፕላኖችን ለገበያ ለማዋል እየጣረ ይገኛል። ታዲያ ይህ የኤርባስ ተግባር ለዴንማርኳ መሪ ያሰቡትን ለማሳካት ተስፋን የሚሰጥ ነው ሲል ቢቢሲ አስነብቧል።
በሀገሬ ቲቪ
2022-01-03
