የፌዴራል የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለተለያዩ ግዢዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን ያወጣሉ። በዚህ የግዢ ሒደት ላይ ሙስና እና አላስፈላጊ የገንዘብ እና የጉልበት ብክነት በሰፊው የሚስተዋልበት እንደኾነ ይነገራል።
መንግሥት ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህን የግዢ ሥርዓት በቴክኖሎጂ ወደ ታገዘ ግብይት እንዲለወጥ ሥራዎችን መጀመሩ ይታወሳል።
ይህም የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት ይባላል። ማንኛውም የፌዴራል የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ግብይታቸውን በዚህ የግብይት ሥርዓት ያደርጋሉ።
በመጀመሪያ ሙከራ ዘጠኝ የፌደራል መሥሪያ ቤቶች ላይ ሙከራ ተደርጎ አሁን 73 ተቋማት ይህን ዘመናዊ የግብይትሥርዓት ተጠቃሚ ሆነዋል የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ የሙከራ ትግብራው ምን ውጤት አስገኘ ስንል ጠይቀናል።
ከዘጠኙ መ/ቤቶች ስድስቱ ሙሉ ለሙሉ ግዢአቸውን በዚሁ ሥርዓት እንዳደረጉ እና ሁለት ተቋማት ግን በአራተኛ ሩብ ዓመት ላይ በሙከራ በማካሄዳቸው ሊሳካ እንዳልቻለ የመንግሥት የግዥ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ ነግረውናል። በተጠቀሰ ዓመት ግዥ ስለማይካሄድበት በማለት መልሰዋል።
የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት ያደጉት ሀገራት ከ 50 ዓመት በፊት ሥራ ላይ አውለውታል ያሉን አቶ ሀጂ በኛ ሀገር መተግበር ከጀመረ በኋላ ጥሩ ውጤት ቢኖረውም አንዳንድ ተቋማት ግን ይህን የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ለመጠቀም እንደማይፈልጉ ሰምተናል።
ግዢው የሚካሔድበት ሶፍትዌር የደህንነቱን ጉዳይ በኢንሳ ክትትል ስር ሲሆን በሀገር ውስጥ ድርጅት የተሰራ መኾኑ ወጪን እንዲቀንስ ማድረጉን በተቋሙ የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት የፕሮጀክት ማናጀር አቶ ታደሰ ከበደ ነግረውናል።
ለሶፍትዌሩ 18 ሚሊዮን ብር ወጪ ኾኗል። አሁን ላይ በ72 ተቋማት እየተተገበረ የሚገኘው የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት በዚህ በጀት ዓመት መንግሥት ከመደበው የበጀት ገንዘብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ለመቀነስ ታቅዶበታል።
በቀጣይ አመታት ከዚህ ከፍ ያለ የገንዝብ ወጪ ይቆጠብበታል። ከዚህ በኋላ የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ የተመዘገቡ የንግዱ ማኀበረሰብ ብቻ ናቸው ምርቶቻቸውን ለመንግስት ተቋማት ማቅረብ እና መጫረት የሚችሉት።
በዚህ ዓመት መጨረሻ ሁሉም ተቋማት በዚህ የግዢ ሥርዓት ተጠቃሚ ይኾናሉ በቀጣይ ደግሞ ወደ ክልል የመንግሥት ተቋማት ተፈጻሚ ይኾናል ተብሏል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-09-30
