ሀገሬ ቲቪ

ባለተሰጣኦው የ3 ዓመት ሕፃን

ልጆች እንደ ነጭ ወረቀት ናቸው፤ በህይወታቸው ሊኖሩት የሚገባውን ብቻ አስተካክለው ፃፉባቸው የሚባለው ያለምክኛት አይደለም።

እድሜ ዘመናቸውን የሚያነቡት ያን በጨቅላ እድሜያቸው የፃንባቸውን ነው እና ነው። መቼስ ሕፃናት ያዩትብም አይደለም ደግመው የሚያደርጉት። የማድረግ ልምምድ ሲበዛ ደግሞ ተሰጣኦ ይሆናል።

ታዲያ ይህን ሁሉ ማንሳታችን፤ ከወደ ቻይና አንድ ጥበበኛ የ3 ዓመት ሕፃን አለ መባሉን ብንሰማ ነው። በቻይና ሃይሎንግጂያንግ ግዛት የሚኖረው ይህ ሕፃን ጋኦ ዩቦ ይባላል። ገና ሦስት ዓመቱ ነው።

ታዲያ በዚህ እድሜው የካሊግራፊ (በቄንጠኛ የመፃፍ ጥበብ) ባለቤት ነው። ይህ ተሰጣኦውም በማህበራዊ መገናኛው ዓለም ውስጥ በርካታ አድናቂዎችን አትርፎለታል።

ማኦቢ የተሰኘውን በሸራ ላይ ለመፃፍ የሚያገለግል ብሩሽን መያዝ በፍጥነት ችሏል። አሁን ሙሉ ትኩረቱን በሸራው ላይ እና በሚስለው የቻይኒኛ ቃላት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

እናቱ የምትሰራቸውን በሸራ ላይ አሳምሮ የመሳል ጥበብ እያየ እንደተማረ የዩቦ እናት ትናገራለች። የመጀመሪያ ቃሉን ገና የ1 ዓመት ሕፃን ሳለ እንደፃፈ፤ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት አስነብቧል።

ልጄ አዳዲስ ቃላቶችንም ሳይቀር ገና ተፅፈው እንዳያቸው ወዲያውኑ ደግሞ ይፅፋቸዋል ስትል እናቱ ተናግራለች።

የዩቦ አጎት ጋኦ ፌንግ አንዲህ ይላል፦

“ብዚ ሰዓቶችን በቤት ውስጥ ፅሑፎችን በመለማመድ ያሳልፋል። በየትኛውም ሰዓት ብሩሹን አንስቶ መፃፍ ይጀምራል። የካሊግራፊ መምህሩ በደንብ ችሎታውን አውጥቶ እንዲያሳይ ረድቶታል። ችሎታውን በደንብ እያሳደገው ሲመጣ ደግሞ የበለጠ እየጎበዘ መጥቷል። እኛም እሱን አይተን ሁሉም ልጅ ውስጥ ማደግ የሚችል ተሰጣኦ እንዳለ አምነናል።”

አሁን ዮቡ 100 የሚሆኑ የቻይኒኛ ፊደላት እና ቃላትን ጠንቅቆ ያውቃል። ችሎታውንም ለሌሎች በማህበራዊ ገፆች ላይ በሸራዎች ላይ እየተጠበበ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመለጠፍ ያጋራል። ከ800 ሺህ የሚልቁ ወዳጆችንም በዚሁ የማህበራዊ መድረክ ተወዳጅቷል።

ማንም ለማህበረሰቡ መልካም ነገርን ማበርከት የፈለገ፤ ልጆቹን እንዲህ ባለው መንገድ ጥበባቸውን እንዲያወጡ ሊያግዛቸው ይገባል። የዩቦ አጎት ጋኦ ፌንግ መልዕክት ነው።

እኛም ይህንኑ እንላለን፤ ማንም ሀገርን ማቅናት የፈለገ በሕፃናት ላይ ያተኩር። ነገን የሚሰሩት እነሱ ናቸው እና።

በሳምሶን ገድሉ
2022-09-30