የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከስልጣን የለቀቅኩት ለዚህች ክቡር ሀገር እድል ለመስጠት ነዉ አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ በፖለቲካዊ አለመግባባት የተነሳ ስልጣናቸውን ለቀዋል። በህዳር ወር ከጦር ኃይሎች ጋር የፖለቲካ ስምምነት የተፈራረሙት ሀምዶክ በትላንትናዉ እለት ምሽት በሱዳን ብሄራዊ ቴሌቭዥን በተላለፈ ንግግር አዲስ ስምምነት ላይ ለመድረስ በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ሀምዶክ በመልዕክታቸዉ ኃላፊነቴን ለመመለስ ወስኛለሁ እናም ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ መልቀቄን ለመግለፅ እፈልጋለሁ ብለዋል። ለዚህች ክቡር ሀገር ለሌላ ሰዉ እድል ለመስጠት ሱዳንን ወደ ሲቪል ዲሞክራሲያዊ ሀገር ለማሻገር እንዲረዳ ይህንን ዉሳኔ ወስኛለሁ ሲሉ በቴሌቭዥን በተላለፈ መልዕክታቸዉ ተናግረዋል። የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለስልጣን ሀምዶክ ከወታደራዊ አስተዳደር ነፃ የካቢኔ መንግስት እንዲቋቋም ባደረጉት ስምምነት በህዳር ወር ላይ ወደ ስልጣን መመለሳቸዉ ይታወሳል። ይህዉ ድርድር ግን የዲሞክራሲ ንቅናቄ በሚያደርጉ አካላት ውድቅ መደረጉ አይዘነጋም። የሀምዶክ ከስልጣን መልቀቅ የሀገሪቱን ፖለቲካ እጣ ፈንታ ወደ ጥርጣሬ ውስጥ ከቷል።
በሀገሬ ቲቪ
2022-01-03
