የ2014 ዓ.ም. የ12ተኛ ክፍል የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ለመስጠት ቅድመዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህንን በማስመልከት የትምህርት ሚንስቴር በዛሬ ዕለት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰትቷል። ፈተናው በሁለት ዙር የሚሰጥ ስለመሆኑም በዚሁ መግለጫ ላይ ተነስቷል።
976,018 ተማሪዎች የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን እንደሚወስዱ የተነሳ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ክልሎች ባደረጉት ጥናት በፀጥታ እና ሌሎች ምክንያቶች 56 ሺሕ የሚሆኑ ተማሪዎች አሁን ፈትናውን አይወስዱም። ይሁን እንጂ ከ1 ወር ባልበለጠ ግዜ ውስይጥ ሁኔታዎች ተመቻችተው እንዲወስዱ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ወደ ሚፈተኑባቸው ዩንቨርሲቲዎች ሲያቀኑ እንደ ሞባይል ስልክ፣ የድምጽ እንዲሁም የምስል መቅረጫ ቁስ፣ ከቴሌ መስመር ውጪ መልእክትን የሚልክ ወይንም የሚቀበል የቴክኖሎጂ ውጤት፣ ኮምፒውተር እና ላፕቶፕ፣ ስማርት ሰዓት፣ እና ሌሎች ማንኛውም ምስል ወይንም ድምፅ መቅረፅ የሚችሉ ቁሶችን ይዞ መገኘት እንደማይችሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል።
በክፍል ውስጥ ሊኖር የሚችል የፈተና ስርቆትን ለመከላከልም ሲባል ፈተናውን የሚሰጡ ፈታኞች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ፈተና በሚሰጥባቸው ዩንቨርሲቲዎች ውስጥ እንዳይገኙ እንደሚደረጉም ሚንስትሩ ተናግረው ከብሔረኝነት እስተሳሰብ የፀዳ ፈተናን ለማድረግ ሌሎች ተግባራት መከናወናቸውንም ሰምተናል።
ፈተናው በዩንቨርሲቲዎች መሰጠቱ የሚጠይቀውን ተጨማሪ ወጪን በሚመለከትም ከምናገኘው ሀገራዊ ጥቅም አንፃር በገንዘብ መለካቱ ትክክል አለመሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ይህንን ብለዋል።
በባለፈው ዓመት ፈተናዎችን ወደ መፈተኛ ቦታዎች በሚጓጓዙበት ወቅት ፈተናዎችን ለመስረቅ በተደረገ ሙከራ 13 የፌደራል ፖሊስ አባላት መገደላቸውን ከመግለጫው ሰምተናል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-10-03
