ሀገሬ ቲቪ

ከሲሚንቶ ንግድ እንዲወጡ የተደረጉ ነጋዴዎች እጣፈንታ

ከወራት በፊት መንግሥት በሲሞንቶ ግብይት ባወጣው መመሪያ መሠረት ሲሚንቶ በማከፋፈል እና ለተጠቃሚው በመሸጥ የተሰማሩ ነጋዴዎች ከገበያው እንዲወጡ ኾነዋል።

በዘርፉ ከጫኚ አውራጅነት እስከ ንግዱ የተሰማሩ ዜጎች ከስራቸው እንዲወጡ መደረጋቸው ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።

በዚህ ጉዳይ ሀሳቡን የሰጠው የከተማዋ ንግድ ቢሮ በበኩሉ አላስፈላጊ እና ረጅም የነበረው የስርጭት መንገድ ተቀየረ እንጂ የሲሚንቶ ንግድ በከተማዋ እንዲቆም አልተደረግም ብሏል።

ቀደም ሲል ለፋብሪካዎች ቅድመክፍያ የከፈሉና ሲሚንቶ ያልተረከቡ ነጋዴዎችም ምርቱን የሚያገኙበት መንገድ እየተመቻቸ እንደኾነ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ተናግረዋል።

እነዚሁ ዜጎች ከሲሚንቶ ንግዱ እንዲወጡ ቢደረግም ሌሎች የግንባታ ቁሶችን የመሸጥ አማራጭ ውስጥ በመግባት የእንጀራ ገመዳቸውን ቀጥለዋል ብለውናል ኃላፊው።

ዳንጎቴ፤ ደርባ፤ ሙገር፤ ኢትዮሲሚንት፤ ካፒታል፤ ኩዩ የተባሉ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለአዲስ አበባ ከተማ ሲሚንቶ እንዲያቀርቡ የተመደቡ ናቸው። ከነዚህ ፋብሪካዎች ከተማዋ በወር 1ሚሊዮን316 ሺ895 ኩንታል በውር ተመድቦላታል።

ከተመደበው ውስጥም ለመንግሥት ግንባታ ከፋብሪካው እየተወሰደ ሲኾን አነስተኛ ቤት የሚገነቡ፣ የሚያድሱ ግለሰቦች ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና ከኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጀት ማከፋፈያዎች ነው መግዛት የሚችሉት።

አነስተኛ ቤትና አጥር የሚገነቡ፤ ቤት ለማደስ የሚፈልጉ ግለሰቦች አሁን ላይ ሲሚንቶን ማግኘት መግዛት ከሚችሉበት ወደ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አምርተን ነበር ኮርፖሬሽኑ ባሉኝ 4 መጋዘኖች ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ግንባታ ለሚያከናውኑ ደንበኞች ሲሚንቶን እየሸጥኩኝ ነው ብሏል።

በከተማዋ ከ22ሺህ ኩንታል በላይ ሲሚንቶ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተገኝቶ እርምጃ መወሰዱን ሰምተናል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-10-04