ሀገሬ ቲቪ

የአ/አ ከተማ የመንገድ ደህንነት ም/ቤት ሪፖርት

የአዲስ አበባ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት በከተማዋ ደህንነት ስትራቴጂ ትግበራ ላይ ውይይት አካሂዷል። ምክር ቤቱ የ2014 በጀት ዓመት አጠቃላይ ሪፖርቱን ያቀረበ ሲሆን በመንገድ ደህንነት ላይ የ13 ዓመት ብሎም የ5 እና ሶስት ዓመታት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።

አዲስ አበባ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ያለባት ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የመንገድ ደህንነት ም/ቤት አስፈልጓታል ያሉት የአዲስ አበባ የመንገድ ደህንነት ም/ቤት ጸሐፊ የሆኑት አቶ ክበበው ሚዴቅሳ የተለያዩ ስራዎች ቢሰሩም አሁንም ቢሆን በከተማዋ በትራፊክ አደጋ ሳቢያ የሞት ቁጥር ከፍ ያለ እንደሆነ ተናግረዋል።

የመንገድ ደህንነት ም/ቤቱ በሪፖርቱ በ2014 በጀት ዓመት በከተማዋ በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች 411 ሞት፣ 1900 ከባድ የአካል ጉዳቶች እና 1213 ቀላል የአካል ጉዳቶች ተመዝግበዋል።

የትራፊክ አደጋዎቹን ለመቀነስም የ13 ዓመት ስትራቴጂ ብሎም የ5 እና ሶስት ዓመት ስትራቴጂዎች ተቀርጸው እየተሰሩ መሆናቸውን አቶ መላኩ ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቶች አካባቢ የፍጥነት መቀነሻ አማራጮችን፣ የእግረኛ መንገዶች እና የመንገድ መብራቶች ላይ በተሰራ ስራ የትራፊክ አደጋዎችን መቀነስ ቢቻልም አሁንም ቢሆን ስራ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በተሰሩት ስራዎች ግን በ100 ሺህ ህዝብ ምጣኔ የሞት ቁጥር ከባለፈው ዓመት አንጻር መቀነስ አሳይቷል ብለዋል ፤ እንደሃገር ያለን የተሽከርካሪ ቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም እየደረሰ ያለው የትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ የመንገድ ደህንነት ም/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ተናግረዋል።

አቶ ምትኩ ከግማሽ በላይ ተሽከርካሪ በአዲስ አበባ የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር በአዲስ አበባ አደጋውን ለመቀነስ ብዙ መስራት ይገባል ብለዋል።

ያለውን የትራፊክ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠን ለመፍታት የህዝብ ትራንስፖርት እና የባቡር ትራንስፖርት ላይ እየተሰራ ነው ያሉን የባቡሩን አቅምስ ለማሳደግ ምን እየተሰራ ነው ላልናቸው አሁን ላይ ያለበትን የአቅም ችግር ለማሻሻል የከተማ አስተዳደሩ ከፌደራል መንግስት ጋር ቅንጅት ፈጥሯል ብለውናል።

የእግረኛ መንገዶችን የሚዘጉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለመቀነስ የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንጻር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመውናል።

በሪፖርቱ በ2014 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 13 ሚሊዮን የትራፊክ ደንብ ጥሰቶች በተዘረጉ አዳዲስ አሰራሮች ተስተናግደዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-10-04