በኑሮ መውጣት መውረድ ውስጥ በስራ ሁኔታ፣ በግል ህይወታችን ሳቢያ፣ ከምንሰማቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ፣ በአካባቢያችን ሁኔታ እንደ ጭንቀት፣ ድብርት፣ ውጥረት የመሳሰሉ ቀለል ያሉ የአዕምሮ ህመሞች ያጋጥሙናል።
እነዚህ ቀለል ያሉ የሚመስሉ የስሜት ጫናዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን ከማወካቸው በተጨማሪ ድግግሞሻቸው እና መጠናቸው ከፍ ያለ የሚሆን ከሆነ ከፍ ወዳለ የአዕምሮ ጤና እክልነት ሊቀየሩ እንደሚችሉም የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
እኛም ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው እነዚህ ቀለል ያሉ የአዕምሮ ህመሞች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ሲገጥሙን ሰዎችን ማማከርን ጨምሮ መፍትሄ ያልነውን እናደርጋለን ሲሉ ገልጸውልናል።
የነዚህ ቀለል ያሉ የሚመስሉ የአዕምሮ ህመሞች ድግግሞሽ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን ከማወካቸው ባሻገር ለመሸሽ በሚል በሚወስዷቸው አማራጮች ወደ ሱሰኝነት ጭምር የሚያመሩ እንዳሉ የስነልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ስለጉዳዩ ሃሳባቸውን የሰጡን የስነ ልቦና ባለሙያ እና መምህር አቶ ሳሙኤል ያሬድ ለመሆኑ መነሻ ምክንያታቸው ምን ሊሆኑ ይችላሉ ላልናቸው በአዕምሯችን ውስጥ ያሉ ኬሚካሎች ማነስ እና መብዛት አንዱ ምክንያት ሲሆን በአዕምሯችን ውስጥ የምናደርጋቸው መብሰልሰሎችም ምክንያት ይሆናሉ ብለውናል።
የአካባቢያችን ሁኔታም ለእነዚህ የአዕምሮ ህመሞች ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የገለጹልን አቶ ሳሙኤል መፍትሄውስ ላልናቸው ደግሞ ህመሞቹ የከፋ ደረጃ ላይ የደረሱ ከሆነ ህክምና አስፈላጊ ሲሆን አካባቢያችንን ብሎም የአኗኗር ዘይቤያችንን ማስተካከል እንደሚገባ ነግረውናል።
በቂ እረፍት መውሰድም ሌላኛው መፍትሄ ስለመሆኑ አቶ ሳሙኤል ያሬድ ነግረውናል።
በአብርሃም በለጠ
2022-10-06
