ሀገሬ ቲቪ

የጨቅላ ህጻናት ሞት ጨምሯል ተባለ

በሀገራችን የጨቅላ ህጻናት የሞት ቁጥር ጨምሯል ሲል የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጨቅላ ህጻናትን የሞት ቁጥር በቀጣይ ሶስት ዓመታት ከግማሽ በላይ የመቀነስ ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል።

ይህንን ያለው የጤና ሚኒስቴር የደረጃ 3 የጨቅላ ህጻናት የጽኑ ህሙማን የህክምና መሳሪያዎች ስርጭት እና ተከላን በተመለከተ ከዩኒሴፍ እና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ባደረገው ምክክር ላይ ነው።

ከሚወለዱ 1 ሺህ ህጻናት 29 ያክሉ ይሞቱ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የሚሞቱት የጨቅላ ህጻናት ቁጥር ከ 1ሺህ ጨቅላ ህጻናት ወደ 33 ከፍ ብሏል ሲሉ የጤና ሚኒስቴር የእናቶች እና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም ገልጸዋል። በዓመት ከ100 ሺህ በላይ የጨቅላ ህጻናት እየሞቱ ስለመሆናቸውም ዶ/ር መሰረት ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጨቅላ ህጻናት ጽኑ ህሙማን የህክምና መሳሪያዎች በ24.2 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ለ80 ሆስፒታሎች እንዲሰራጩ ስለመደረጋቸው ጠቁመዋል።

ከፍተኛ አቅም ያላቸውን የህክምና መሳሪያዎቹን ከየዞኑ ለአንድ ሆስፒታሎች እንዲዳረሱ ተደርጓል። የህክምና መሳሪያዎቹ የጨቅላ ህጻናት ላይ የሚደርስ ሞትን እና የአካል ጉዳትን ለመቀነስ የሚያግዙ ናቸው ተብሏል።የህክምና መስሪያዎቹን ከመጠቀም አንጻር ለ400 ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል።

እንደጤና ሚኒስቴር በተሰሩ ስራዎች የእናቶች እና ህጻናት ሞትን መቀነስ ቢቻልም የጨቅላ ህጻናት ሞት ግን አሁንም ጨምሯል። የጨቅላ ህጻናትን ሞት እንደሞት ያለመቁጠር እና የእናቶችንም ሞት መደበቅ እንዳለም ተጠቁሟል።

ለሆስፒታሎቹ የተሰራጩ ከፍተኛ አቅም ያላቸውን የህክምና መሳሪያዎች በባለቤትነት እና ኃላፊነት መጠቀም እንደሚገባም ተገልጿል።

በአብርሃም በለጠ
2022-10-11