የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ የተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች ከተወሰነው ታሪፍ በላይ እያስከፈሉን ነው ሲሉ ተገልጋዮች ቅሬታቸውን ገለጹ።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር በበኩሉ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነውም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ ከሆነ ከመስመር እስከመነሳት የሚያደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ብሏል።
ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች የድጎማ ስርዓት ተጠቃሚ እንደሆነ የሚገልጽ ጽሁፍን(ስቲከር) የለጠፉ ተሽከርካሪዎች አሽከርካሪዎች እና ረዳቶች ከታሪፉ በላይ እያስከፈሉን ነው ብለውናል።
ስለጉዳዩ ምላሽ የሰጡን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አቶ ታጠቅ ነጋሽ እስካሁን ከ163 ሺህ በላይ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ከ1 ሺህ በላይ በሚሆኑ የነዳጅ ማደያዎች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለውናል።
አቶ ታጠቅ ምንም እንኳን ለሁለተኛ ጊዜ የነዳጅ ጭማሪ ቢደረግም የድጎማ ስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑት ተሽከርካሪዎች ነዳጅ እንዲቀዱ እየተደረገ ያለው አስቀድሞ በነበረው የነዳጅ ዋጋ በመሆኑ የታሪፍ ጭማሪ ሊያደርጉ እንደማይገባ ነግረውናል።
የነዳጅ ጭማሬውን ወጭ መንግስት እየቻለላቸው ሳለ የታሪፍ ጭማሪ የሚያደርጉ አሽከርካሪዎች ላይ ከመስመር እስከመነሳት የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ብለውናል።
ህብረተሰቡ በትራንስፖርት ዋጋ መጨመሩ እንዳይጎዳ በማለም የድጎማው ተጠቃሚነታቸውን የሚገልጽ ስቲከር ለጥፈው ተሽከርካሪዎቹ እንዲንቀሳቀሱ በመደረጋቸው ማህበረሰቡ ከተወሰነው ታሪፍ በላይ ባለመክፈል መብቱን ሊያስከብር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለዚህም ህብረተሰቡ ሊተባበር ይገባል ያሉ ሲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጸጥታ አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለውናል።
በአብርሃም በለጠ
2022-10-12
