የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከግብርና ሚንስቴር ጋር የግብርናው ዘርፍ ለሀገር በሚጠቅም መልኩ እንዲሆን ለማድረግ ያስችል ዘንድ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልን ለማፍራት የሚያስችል መግባቢያን ተፈራረሙ።
በሀገራችን ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የግብርናው ዘርፍ በተለምዷዊ መንገዶች መመራቱ ሀገር ልታገኝ የሚገባትን እንዳታገኝ ሲያደርጋት መቆየቱን በርካቶች ይስማሙበታል።
ታዲያ በዘርፉ የሰለጠነ እና ክህሎት ያለውን የሰው ኃይል መፍጠር በቀጣይ ሚኒስቴር መስሪያቤቶቹ የሚከውኗቸው ተግባራት መሆናቸውን ከፊርማ ስነስርዓቱ ሰምተናል።
እምቅ አቅም ያለውን የግብርናው ዘርፍ መገኘት ባለበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የሁሉም ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ያነሱት የግብርና ሚንስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን ሸፍኖ ወደ ውጪ ለመላክ እየተደረገ ያለው ጥረት ሊታገዝ የሚገባው መሆኑን አንስተዋል።
ዛሬ የተደረገው ስምምነትም በክህሎት በኩል ያለውን ክፍተት መሙላት የሚችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ግብርናን እስካሁን በመራንበት መንገድ መምራት አንችልም ያሉት ሚንስትሩ እያደገ ያለውን የሰው ኃብት ለመመገብ ግብርናውን በቴክኖሎጂ ማገዝ እና ክህሎት ባለው የሰው ኃይል መሙላት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ነው ስምምነት ያደረግነው ብለዋል።
ዛሬ የተደረገው የስምምነት ፊርማ፣ ላለፉት ስድስት ወራት በጋራ ሊሰሩባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በባለሙያዎች ጥናት ሲደረግበት የቆየ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ትግበራ የሚገባበት መሆኑን ሰምተናል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-10-12
