ሀገሬ ቲቪ

የዓለም ኢኮኖሚ ከባድ አደጋ ተጋርጦበታል

የዋጋ ግሽበት፤ የኃይል ዋጋ ማሻቀብ የዓለምን ኢኮኖሚ ወደ ውድቀት እየመራ መኾኑን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ በሪፖርቱ አመላክቷል።

በጦርነት፣ በተለያዩ ሀገራት የወለድ ምጣኔ እየጨመረ መምታቱ የዋጋ ግሽበት፣ የኃይል እና የምግብ ዋጋ ለዜጎች የሚቀመስ መኾን እንዳይችሉ አድርጓል ብሏል ድርጅቱ በሪፖርቱ።

ይህ ብቻ አይደለም በዓለም አቀፍ ደረጃ የፋይናንስ እና የምጣኔ ሀብቱ ላይ ከፍተኛ አደጋ እንዲደቀንበት ኾኗል። ምንአልባት እንደ አሜሪካ ፣ ቻይና እና የአውሮፓ ሀገራት ያሉ ጠንካራ ኢኮኖሚ አላቸው የሚባሉ ሀገራት ይህን ፈተና ሊቋቋሙ ይችሉ ይኾናል ሲሉ በተቋሙ የሚሰሩ የኢኮኖሚ ምሁራን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ የዜጎችን ሕይወት እየፈተነ ያለው የዋጋ ግሽበት ገና ከዚህም በላይ መባሱ አይቀርም ብለዋል። በ2023 ይህ ችግር ሊጎላ እንደሚችል ተጠቁሟል።

የአሜሪካ ኢኮኖሚ ከከፍተኛ ወለድ ጋር እየታገለ መሆኑ፣ የተፈጥሮጋዝ ዋጋ እና ነዳጅ መጨመር በአውሮፓ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መቀጠሉ፣ በኮቪድ 19 ቫይረስ ምክንያት ከ 2 ዓመት በላይ የአንቅስቃሴ ገደብ በቻይና አሁንም ሳይነሳ መቆየቱ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ከሥራ ውጪ ኾነዋል እነዚህ የተጠቀሱት ችግሮች የዓለም ኢኮኖሚ ከፊቱ አስፈሪ አደጋ እንዲጋረጥበት አድርጓል ሲል አይ ኤም ኤፍ በሪፖርቱ ጽፏል።

በሐምሌ ወር በ2023 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖረው ምርት እድገት 2.9% ይኾናል ተብሎ ተተንብዮ ነበር። አሁን ግን ይህን ትንበያውን በማውረድ የቀጣይ ዓመት የዓለም ኢኮኖሚ 2.7% ይኾናል ብሏል።

ያለፈው ዓመት በተለይም የኮቪድ 19 የተወሰዱ እርምጃዎች እየቀለሉ መምጣታቸውን ተከትሎ የዓለም ኢኮኖሚ 6% እንደነበር በ2022 ግን ወደ 3.2 በመቶ ዝቅ እንደሚልም አሳውቋል።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የገንዘብ እና የካፒታል ማርኬት ዳይሬክተር የኾኑት ቶቢያስ አድሪያን ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ወይይት ዓለም ኢኮኖሚ እንዲህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ መቼ ገባ የሚለውን በሙሉ አንደበት ለመናገር ይቸግራል ይህን ለመመለስ ምን አልባትም አስር ዓመታትን ወደ ኋላ መሔድ በዓለም ላይ ተከስተው የነበሩ በርካታ ጦርነቶችን መመልከት አለብን ብለዋል። በዚው ልክ የነበረውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንዲሁ መፈተሽ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-10-14