ፌልትማን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ሐሙስ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማ ኢትዮጵያ የሚመጡት ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር በሰላም ድርድር ጉዳይ ለመነጋገር እንደሆነ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ አስታውቀዋል፡፡ አምባሳደር ፌልትማን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ቢገለፅም እነማንን እንደሚያገኙ ምንም የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡ አምባሳደሩ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ወደ ትግራይ ክልል ይሄዱ እንደሆነ ፕራይስ ተጠይቀው፤ ለአሁን መናገር የሚችሉት አምባሳደሩ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማ ከዚህ ቀደም የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላማዊ መንገድ ይፈታ በሚል በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይታወቃል፡፡ ቃል አቀባዩ በውይይቱ ዝርዝር ላይ መናገር የሚችሉት በማጠቃለያው እንደሆነ እና ዝርዝሩንም በፅሁፍ እንደሚያወጡ ገልፀዋል ሲል የአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ዘግቧል፡፡ ፕራይስ አምባሳደር ፌልትማን ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ አሁን ያለው ሁኔታ አመቺ መሆኑን ጠቁመው ሁለቱም ወገኖች ውጊያ እንዲያቆሙና ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲቀርቡ ዕድል እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡ አምባሳደር ፌልትማን ኢትዮጵያ ሲገቡ የውይይቱ ይዘት ይኸው እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
በሀገሬ ቲቪ
2022-01-05
