ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብረታብረት እና የብረት ምርት ግብአቶችን ከውጪ ለማስገባት ከ2.5 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች።
ሀገሪቱ አሁን ባለችበት የዕድገት ጎዳና የኮንስትራክሽን እና የኢንዱስተሪ ዘርፉ ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ ወጪው በየጊዜው እንደሚጨምር ይጠበቃል ።
በመሆኑም ይህን ከፍተኛ የወጪ ምንዛሬ ለማስቀረት በተለያዩ ተቋማት ከ አገልግሎት ውጪ የሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ የማያገለግሉ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን በድጋሜ ጥቅም ላይ ለማዋል መወሰኑን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል።
የመንግስትም ሆኑ የግል ተቋማት ያገለገሉ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች እና በውዳቂ ብረታ ብረትነት የሚወገዱ ማሽነሪዎችን በ51.25 ብር ቁርጥራጭ የሆኑ ብረታ ብረቶችን በኪሎ 64 ብር እንዲሁም የካስት አይረን ብረቶችን በ51.75 ብር ለብረታ ብረት አቅላጭ ኢንዱስትሪዎች ብቻ እንዲሸጡ የጠቆሙት ሚኒስትሩ ከየ ተቋማቱ የሚሰበሰቡ ብረቶች ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚወጡትን የወጪ ምንዛሬዎች ያስቀራሉ ብለዋል።
ይህ ጥረቱን በጊዜያዊነት ለመፍታት የተወሰደ እርምጃ ሲሆን ሀገሪቱ ያላትን የብረት ሀብት በዘላቂነት እንድትጠቀም ለማስቻል በተለዩ አካባቢዎች ጥናት እያኬሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በዮሴፍ ከበደ
2022-10-14
