ሀዲስ ዓለማየሁ ደራሲ፣ ከፍተኛ ባለስልጣን ብሎም ዲፕሎማት በመሆን ሀገራቸውን ያገለገሉ ታላቅ ሰው ናቸው።
እኒህ ሰው ምንም እንኳን በሀገራችን ተወዳጅነትን በማትረፍ ቀዳሚው በሆነው የልቦለድ ስራቸው ፍቅር እስከ መቃብር ቢታወቁም፣ የእልም ዣት፣ ወንጀለኛው ዳኛ የተሰኙ የልቦለድ ስራዎችን ብሎም የተውኔት ስራዎችን ያበሻ እና የወደ ኋላ ጋብቻ፣ ኢልቦለዳዊ መጻህፍትንም ትዝታ፣ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል? ተረት ተረት የመሰረት የመሳሰሉ ስራዎችን አበርክተዋል።
እኒህ በመንግስት አገልግሎትም፣ በድርሰቱ ዓለምም ኢትዮጵያን ያገለገሉት ሰው የተወለዱት በዛሬዋ ዕለት ጥቅምት 7፣ 1902 ዓ.ም. ነበር።
ሀዲስ ዓለማየሁ በ20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት፣ ደብረ ማርቆስ አውራጃ፣ በጎዛምን ወረዳ ከየኔታ ዓለማየሁ ሰለሞን እና ወ/ሮ ደስታ ዓለሙ ነበር የተወለዱት። ሀዲስ ገና ልጅነታቸው የዘመኑን የቤተክርስቲያን ትምህርት ተከታትለዋል።
በአባታቸው ሀገር ደብረ ኤልያስ ግዕዝን ተምረዋል፤ ቅኔን ተቀኝተዋል። የቤተክርስቲያን ትምህርትን ከደብረ ኤልያስ በተጨማሪ በዚያው በጎጃም በደብረ ወርቅ እና ዲማ ቀስመዋል።
በ1918 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት ሀዲስ በስዊዲን ሚሽነሪ ትምህርት ቤት ኋላም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በጣሊያን ወረራ መዳረሻ በመምህርነት ብሎም በጉምሩክ ባለሙያነት ሰርተዋል።
በሁለተኛው የጣሊያን ወረራም የልዑል ራስ አምሃ ኃ/ሥላሴ ጦርን ተቀላቅለው በአርበኝነት ሲዋጉ ቆይተው በምዕራብ ኢትዮጵያ በጣሊያን ተማርከዋል። ለሰባት ዓመታት በግዞትም በፖንዞ ደሴትና በሊፓሪ ደሴት ታስረው ቆይተዋል።
የአላይድ ኃይሎች ካስመለጧቸው በኋላ በ1936 ዓ.ም. ደግሞ በነጻነት ተመልሰዋል። በትምህርታቸው እንደገና በኦክስፎርድ ከገፉ በኋላ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በተለይም በትምህርት ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል።
ሀዲስ ከነጻነት በኋላ ኢትዮጵያን በማደራጀት ሂደቱ ተሳታፊ ነበሩ። በማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብሎም በእየሩሳሌም፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በእንግሊዝ በዲፕሎማትነት ሀገራቸውን አገልግለዋል።
ሀዲስ ዓለማየሁ በወርቃማ የስልጣን ጊዜያቸው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) በመዲናችን አዲስ አበባ እንዲመሰረት አስተዋጽኦ ነበራቸው።
የሰሯቸውን ስራዎች በአጭር ቅደም ተከተል ዘርዝሮ መጨረስ ባይቻልም መምህር፣ ደራሲ፣ አርበኛ፣ ሚኒስቴር፣ ዲፕሎማት የሆኑት እኒህ ሰው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በመንግስት ኃላፊነት ከ1953ቱ መፈንቅለ መንግስት በኋላ እስከ 1961 ዓ.ም. በሚኒስቴርነት ማዕረግ አገልግለዋል።
የሚኒስትሮች ም/ቤት የመማክርት ጉባኤ አባል ከ1961 - 1966 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በሀገሪቱ ፓርላማ የህግ መወሰኛ ም/ቤት አባል ኋላም ከ1966 - 1968 ዓ.ም ደግሞ የጎጃም ሕዝብ በመረጣቸው መሰረት የብሄራዊ ሸንጎ አባል ሆነው አገልግለዋል።
ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል? በሚለው መጽሃፋቸው ለሀገራቸው ምን ዓይነት አስተዳደር እንደሚያስፈልጋት ሀሳባቸውን የገለጹት ሀዲስ ዓለማየሁ ደርግ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው እንዲያገለግሉ ጠይቋቸው ነበር። ይሁንና ግን ምላሻቸው አይሆንም የሚል ሆኗል።
የመንግስት ኃላፊነት ድርሰትን ከመጻፍ ያላገዳቸው ታላቅ ደራሲም ናቸው፤ በሚኒስቴርነት እና ዲፕሎማትነት ዘመናቸው ሳይቀር ጽፈው መጻህፍትን አበርክተውልናል።
የመጀመሪያ የተውኔት ድርሰታቸው ከሆነችው በ1929 ዓ.ም. ያበሻ እና የወደኋላ ጋብቻ ጀመሮ በ1948 ዓ.ም. ተረት ተረት የመሰረት ወግን፣ በ1958 ዓ.ም. ፍቅር እስከ መቃብርን፣ በ1974 ዓ.ም. ደግሞ ወንጀለኛው ዳኛን እና ሌሎችም የታተሙ እና ያልታተሙ ስራዎቻቸውን እንካችሁ ብለውናል።
በፍቅር እስከ መቃብር ከጣሊያን ወረራ በኋላ የተዘነጋውን የሀገራችንን የባላባት ስርዓት ገጽታ በፍቅር እና ስነ ጽሁፋዊ ውበት በማንጸባረቅ የኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ አባት እስከመባል ደርሰዋል።
በ1960 ዓ.ም. የቀ.ኃ.ሥ ሽልማትን በስነጽሁፍ ዘርፍ ያገኙ ሲሆን በ1991 ዓ.ም. ደግሞ ከአ.አ.ዩ. የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል።
ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ በ94 ዓመታቸው አርፈዋል።
በአብርሃም በለጠ
2022-10-17
