የመከላከያ ሰራዊት የሽረ ከተማን መቆጣጠሩን የሕወሃት ቡድን ባወጣው መግለጫ አስታውቀ። ሮይተርስም ሁለት የዲፕሎማቲክ እና ሰብዓዊ ተቋማት ምንጮች ሆኑኝ ብሎ እንደዘገበው መከላከያ ሰራዊት የሽረ ከተማን በትላንትናው ዕለት ተቆጣጥሯል።
የኢፌዲሪ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫው የሀገሪቱን የአየር ክልል ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በትግራይ ክልል የሚገኙ የአየር ማረፊያዎችን፣ የፌደራል ተቋማትን ብሎም ትልልቅ መሰረተ ልማቶችን የመጠበቅ ተግባርን እከውናለሁ ብሏል።ይሁን እንጂ ሽሬን በቁጥጥሩ ስር ስለ ማዋሉ ያለው ነገር የለም።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የሕወሃት ቡድን የአፍሪካ ህብረት በድጋሜ ላቀረበው የሰላም ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ ቢሆንም ጦርነቱ ግን ጠንከር ስለማለቱ ነው የሚገለጸው።ጉዳዩን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደርጉት የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው ብለዋል።
“በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከሚባለው በላይ ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል። ግጭቱና ጥፋቱ እየተባባሰ ነው የመጣው።ማህበራዊ ውድመቱም እንደዛው ሰለዚህ በሺትዮጵያ መንግስትና በሕወሃት ቡድን መካከል ያለው ግጭጥ አሁን ሊቆም ይገባል።በጦረነት የሚመጣ አንዳች መፍትሄ የለም።”
አንቶንዮ ጉተሬዝ በየቀኑ ሲቪል ዜጎችን እየገደለ ሺዎችን እያፈናቀለ ነው ያሉ ሲሆን ተፋላሚ ኃይሎች በአስቸኳይ ጦርነቱን እንዲያቆሙ እና በአፍሪካ ህብረት ወደ ተጀመረው የሰላም ውይይት እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
በጦርነቱ ሳቢያ ለሰባት ሳምንታት የሰብዓዊ ድጋፍ እንደተቋረጠ የነበረ የገለጡት ጉተሬዝ አፋታኝ መፍትሄ ያሻል ብለዋል።
መንግስት በበኩሉ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሰብአዊ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲደርስ አደርጋለሁ ያለ ሲሆን ጦርነቱ በከተሞች እንዳይደረግ ጥንቃቄ እንደሚያደርግም አስታውቋል።
መንግስት በትግራይ ክልል የሚገኙ አየር ማረፊያዎችን እና ተቋማትን እንደሚቆጣጠር ቃል ከመግባቱም በተጨማሪ በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብሏል።
በአብርሃም በለጠ
2022-10-18
