በኢትዮጵያ ያሉ የቤት ሰራተኞች ተገቢውን ደሞዝ በወቅቱ እንደማያገኙና የስራ ሰዓታቸው እንደማይጠበቅ አንድ ጥናት አመላከተ።
ጥናቱ አብዛኞቹ ሰራተኞች ዕድሜያቸው ከ 18 ዓመት በታች እንደሆነም አስታውቋል ። ጥናቱ በፍሪደም ፈንድ እና በፖፑሌሽን ካውንስል የተደረገ ነው።
በዓለማችን 17.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናት እና ወጣቶች በቤት ውስጥ ሰራተኝነት እንደሚያገለግሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እንደሆኑም ይታመናል።
በሀገራችም በቤት ውስጥ ስራ ከተሰማሩት ሴቶች አብዛኞቹ ከ15 ዓመት በታች ስለመሆናቸው ይነገራል።
በቤት ሰራተኝነት ላይ በተሰማሩ ሴቶች ላይ የተሰራ ጥናት ይፋ ተደርጓል። አዲስ ከተማ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ጉለሌ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ጥናቱ መደረጉን በመድረኩ ተነግሯል።
ከ12 እስከ 18 ዓመት ያሉ በቤት ውስጥ ሰራተኝነት እያገለገሉ ባሉ ልጆች ላይ የተሰራው ይህ ጥናት እንደሚጠቁመው ከሆነ 88 በመቶ የሚሆኑት ልጆች በሀገሪቱ ካሉ የገጠር አካባቢዎች የፈለሱ ናቸው።
ከእነዚህ ውስጥ 67 በመቶ የሚሆኑት እራሳቸውን እንደ ሩቅ ቤተሰብ እንጂ እንደቤት ሰራተኛ የሚመለከቱ ዓለመሆናቸውን ጥናቱ ጠቁሟል።
ከእነዚሁ መካከልም 52 በመቶ የሚሆኑት ምንም አይነት ክፍያ የማያገኙ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ የወር ደመወዛቸው በአሰሪዎቻቸው እጅ እንደተቀመጠ የሚነገራቸው እና ለቤተሰባቸው እየተላከላየውቸው ያሉ ናቸው ተብሏል።
በኢትዮጵያ እድሜያቸው ለስራ የደረሱ ተብለው የሚታሰቡ ከ15 እስከ 17 ዓመት ድረስ የሆናቸው ልጆች በሳምንት ለ42 ሰዓት እንዲሰሩ ቢደነገግም በጥናቱ የተገኘው ውጤት እጅጉን ከዚህ የራቀ ስለመሆኑ ተነግሯል።
በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ጥቂት መሆን እና በሕፃናት የቤት ውስጥ ሰራተኞች ላይ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን ለችግሩ መስፋት እንደምክያት እንደሚጠቀስ ያነሱት አቶ ዳናኤል ግንዛቤን ከመፍጠር ባለፈ መሰራት ያለባቸው ስራዎች ስለመሆራቸው ጠቁመውናል።
በዮሴፍ ከበደ
2022-10-19
